Fana: At a Speed of Life!

መስሪያ ቤቶችን ዘመናዊና ምቹ በማድረግ ለሕዝባችን ቀልጣፋ አገልግሎት እንሰጣለን – አቶ ሙስጠፌ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ የጀረር ዞን እና የደጋህቡር ከተማ አስተዳደር አዳዲስ ጽህፈት ቤቶችን መርቀው ከፍተዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ አቶ ሙስጠፌ እና የክልሉ ም/ቤት አፈ ጉባዔ አያን አብዲን ጨምሮ የክልሉ አመራሮች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የተመረቁት ዘመናዊ ሕንጻዎች የተለያዩ የስራ ክፍሎች፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ ካፍቴሪያ እና የሰራተኛ ማዕከላት ያላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

አቶ ሙስጠፌ÷ ሕዝቡ ከመንግስት የሚፈልገውን አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ ዘመናዊና ለስራ ምቹ የሆኑ ስፍራዎች አስፈላጊ ናቸው ብለዋል፡፡

ለዚህም በሁሉም የክልሉ ዞኖች ዘመናዊ ጽህፈት ቤቶች መገንባታቸውን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት፡፡

የጽህፈት ቤቶቹ መገንባትም የሰራተኛው የስራ መንፈስ ከፍ እንዲል እና ለሕዝብ የሚሰጠው አገልግሎት ዘመናዊና ቀላል እንዲሆን ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ከምረቃው ጎን ለጎንም አቶ ሙስጠፌ በደጋህቡር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸው ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በ120 ሚሊየን ብር ወጪ ለሚገነባ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.