Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ለ159 የክህሎት፣ ቴክኖሎጂ እና የሥራ ፈጠራ ሐሳብ ተወዳዳሪዎች እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተካሄደው የክህሎት፣ ቴክኖሎጂ እና የሥራ ፈጠራ ሐሳብ ውድድር ለ159 ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል፡፡

“የክህሎት ማዕበል ለኦሮሚያ ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ ክልል አቀፍ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የሥራ ፈጠራ ሐሳብ እና የተግባራዊ ጥናት እና ምርምር ውድድር ማጠቃለያ እና የዕውቅና መስጫ መርሐ-ግብር በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በ4ኛው ክልል አቀፍ ውድድር 573 የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን÷ 159ኙ ዕውቅና ማግኘታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር ) እንደገለጹት÷ መንግሥት የክህሎት ልማት ቀጣይነት ላለው ዕድገተ እና ብልጽግና ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው።

እንደ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው ክልል አቀፍ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የሥራ ፈጠራ ሐሳብ እና የተግባራዊ ጥናት እና ምርምር ውድድር ላይ የሚቀርቡ ቴክኖሎጂዎች ቁጥር እና ጥራትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኦሮሚያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ሰቦቃ እንዳስታወቁት÷ በክልል ደረጃ የተካሄደው የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የሥራ ፈጠራ ሐሳብ እና የተግባራዊ ጥናት እና ምርምር ውድድር በርካታ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች የታዩበት ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.