Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅሟ 5 ሺህ 200 ሜጋ ዋት መድረሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅሟ 5 ሺህ 200 ሜጋ ዋት መድረሱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ አስታወቀ፡፡

በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት ሽፋን ወደ 96 በመቶ ለማድረስ መታቀዱም ነው የተገለጸው፡፡

በዘርፉ የኃይል ማመንጫዎች ስትራቴጂና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ማርዓለም አምደብርሃን እንዳስታወቁት ÷በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የኢኮኖሚውን ፍላጎት ማሟላት የሚችል ኃይል ከውሃ ፣ ከንፋስ ፣ ከፀሀይ እና ከከርሰምድር እንፋሎት ለማመንጨት ታቅዷል።

በአሁኑ ወቅትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም 5 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ደርሷል ነው ያሉት፡፡

የዜጎች ኤሌክትሪክን የመጠቀም ፍላጎት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ይህንን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ተቋሙ ከተለያዩ ታዳሽ የኃይል ምንጮች አዳዲስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በመገንባት ሀገራዊ ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ሀገሪቱ ለወጠነቻቸው የልማት ግቦች ስኬት የሚያግዝ ጥራት ያለውና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለማቅረብ በትኩረት እየሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.