Fana: At a Speed of Life!

በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ 15 ግለሰቦች ላይ ፖሊስ ምርመራውን እንዲያጠናቅቅ የ14 ቀን ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ 15 ግለሰቦች ላይ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ እንዲቀርብ የ14 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

መርማሪ ፖሊስ ሕገ መንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለማፍረስ በማሰብ በኢ – መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ነበሩ ባላቸው 15 ተጠርጣሪዎች ላይ ነው ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ የ14 ቀን ጊዜ የፈቀደው።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የፖሊስን የጥርጣሬ መነሻ ዝርዝር እና የተጠርጣሪዎችን መከራከሪያ ነጥብ ባሳለፍነው ዓርብ ዕለት በነበረ ቀጠሮ መመልከቱ ይታወሳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ  ዳዊት አባቡ፣ በቀለ ሃይሌ (ዶ/ር)፣ ጌታቸው ጥዑመ ልሳን፣ ሃብታሙ ዳኜ፣ ትዕዛዙ ታረቀኝ፣ምስጋናው ማሩ፣ ሙሉቀን ወንዴ፣ ቴድሮስ ተሾመ፣ጌታወይ አለሙ፣ጌትነት ወንደሰን፣ሰይፈ ተስፋዬ፣ ጌታቸው ወርቄ፣ አንደበት ተሻገር፣ ታደሰ ወዳይነህ እና ማስረሻ እንየው  ይባላሉ።

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ተጠርጣሪዎቹ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት  ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመቀየር በማሰብ፣ ስትራቴጂክ ሰነድ በማዘጋጀት፣ የፖለቲካ ክንፍ፣የወታደራዊ አደረጃጀትና የስልጠና ክንፍ፣ የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ክንፍ፣የኢንተለጀንስ መረጃ ክንፍ እና ሌሎች የድርጊት መርኃ ግብር አፈጻጸም በማውጣት  እስከ ታች መዋቅር በመዘርጋትየስራ ክፍፍል ስምሪት ማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡

በተጨማሪም ታጣቂ ኃይል በመመደብ፣ በማደራጀት እና መሳሪያ በማስታጠቅ  በትጥቅ የታገዘ ህዝባዊ አመፅ በመቀስቀስ እና በማሳመፅና  የስራ ማቆም አድማ መቀስቀስ የሚሉ የሽብር ወንጀል  የጥርጣሬ መነሻዎች ናቸው  ያላቸውን ነጥቦች ጠቅሶ  ማቅረቡም የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም መርማሪ ፖሊስ ባቀረበው የጥርጣሬ መነሻ ዝርዝሩ ውስጥ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሆኑ ወጣቶች፣ተማሪዎች እና በሕገ-ወጥ መንገድ አደራጅተዋቸዋል ባላቸው  ታጣቂዎች  የፖለቲካ ቅስቀሳ በማድረግ ስልጠና በመስጠትና በማሰልጠን ፣ለሽብር ወንጀል ድርጊት የሚውል ገቢ እንዲሰበሰብ በማስተባበር በተደረገ የሽብር ወንጀል መምራት ተግባር ፣ በርካታ ንፁሃን ዜጎች ህይወት ማለፉን እና ንብረት መውደሙን ጠቅሶ የጥርጣሬ መነሻውን አቅርቧል።

በዚህ መልኩ ፖሊስ ያቀረበውን የጥርጣሬ መነሻ ዝርዝር የደረሳቸው ተጠርጣሪዎቹ በተጠቀሰው የሽብር ተግባር ተሳትፎ እንደሌላቸው ጠቅሰው ተከራክረዋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ ” ከዚህ በፊት በሌላ ፍርድ ቤት ሁከትና አመፅ መቀስቀስ በሚል መነሻ  ተጠርጣሪዎቹ በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ምርመራ ሲደረግባቸው እንደነበር አንስተዋል፡፡

”በነዚህ ጊዜያት  የተሳትፎ ደረጃቸው ተለይቶ እንዲቀርብ የተሰጠው ትዕዛዝ ሳይተገበር በድጋሚ የሽብር ወንጀል ተብሎ መቅረቡ አግባብ የለውም ” ሲሉ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ እንደማይገባ ጠቅሰው ተከራክረው ነበር።

በተጨማሪም ጠበቃው ተጠርጣሪዎቹ የቤተሰብ አስተዳደሪ መሆናቸውን በመጥቀስ የዋስ መብታቸው እንዲከበር ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ተጠርጣሪ  በቀለ ኃይሌ (ዶ/ር) እና ተጠርጣሪ ማስረሻ እንየው ያጋጠማቸውን የጤና እክል በመጥቀስ ያሉበት የጤና ሁኔታ  ታሳቢ እንዲደረግላቸው አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ” በማንነታችን ምክንያት ነው የታሰርነው” የሚሉ ሃሳቦችን ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡ ተጠርጣሪዎችም ነበሩ።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ÷ ”ማንም ሰው በማንነቱ ታስሮ አያውቅም፤ ሊታሰርም አይችልም”ሲል መልስ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ በፊት በተጠረጠሩበት የሁከትና ብጥብጥ ማስነሳት ወንጀል በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ምርመራ ሲደረግባቸው እንደነበር የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ÷  በዚህ በተደረገ ምርመራ በሽብር ወንጀል ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያመላክቱ የመነሻ ማስረጃዎችን በማግኘታችን   ምክንያት ነው በሽብር መዝገብ  ያቀረብናቸው በማለት ለችሎቱ አብራርቶ ነበር።

ከጤና ጋር ተያይዞ ለተነሳ አቤቱታ መርመሪ ፖሊስ ”በቂ የህክምና ባለሙያዎች ስላሉን ይህ አያሳስብም ”ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

 

በዚህ በተጀመረው የሽብር ወንጀል መዝገብ የሚቀሩ ማስረጃዎችን ሰብስበን ለመቅረብና መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ አጠናቀን ለሚመለከት አካል ለመላክ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገናል በማለት ተከራክሮ ነበር።

 

የተጠርጣሪዎችን መከራከሪያ ነጥብና የፖሊስን የጥርጣሬ መነሻ መዝገብ የመረመረው ፍርድ ቤቱ ተገቢውን ትዕዛዝ ለመስጠት ለዛሬ ከሰዓት በኃላ በያዘው ቀጠሮ መሰረት የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ በማድረግ ፖሊስ የጀመረውን ምርመራ አጠናቅቆ እንዲቀርብ የ 14 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

 

ዛሬ የተፈቀደው ጊዜም  ካሳለፍነው ዓርብ ዕለት ማለትም ከግንቦት 4 ቀን ጀምሮ ታሳቢ የሚደረግ መሆኑን ፍርድ ቤቱ አሳስቧል።

 

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.