Fana: At a Speed of Life!

26 ቢሊየን ብር በመመደብ የመብራት መቆራረጥ ችግርን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የመብራት መቆራረጥ ችግር ለመቅረፍ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ 26 ቢሊየን ብር ተመድቦ የማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ÷ ሁሉንም መስመሮች በአንድ ጊዜ ማዳረስ ስለማይቻል በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ መጋቢ መስመሮችን ትኩረት በማድረግ የ10 ቢሊየን ብር በጀት ተመድቦ የማሻሻያ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አሮጌ የነበሩ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት የመቀየር እንዲሁም ኮንዳክተሮችን በከፍተኛ እና አቅም ባላቸው የመተካት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የመልሶ ግንባታ ሥራው ከአዲስ አበባ ውጪ በአዳማ ፣ በባሕርዳር እንዲሁም በሌሎች ሥምንት የክልል ዋና ዋና ከተሞች እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በተጨማሪም በሐረር ፣ በሻሸመኔ ፡ በወላይታ ፡ በጎንደር ፡ በደብረማርቆስ እና በኮምቦልቻ ከተሞች እየተካሄደ የሚገኘው ግንባታ 70 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡

በቅርቡም በተለያዩ 10 ትላልቅ የዞን ከተሞች የማሻሻያ ሥራዎች ይሰራሉም ነው ያሉት።

በተለይ በክረምት ወቅት የሚያጋጥመውን የኤሌክትሪከ መቆራረጥ ችግር ለመቅረፍ ከወዲሁ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ፍተሻ እና የጥገና ሥራዎች እየተከወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.