Fana: At a Speed of Life!

የጉበት ካንሰር መንስኤ ፣ መከላከያ መንገዶችና ህክምናው

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጉበት በሆድ የላይኛው ክፍል በስተቀኝ በኩል የሚገኝ ሲሆን የንጥረ ነገሮችን ሂደት የሚያስተካክል፣ ደምን የሚያጣራ እና ኢንፌክሽንን የሚዋጋ የሰውነት አካል ነው።

የቀዶ ህክምና ሰብ እስፔሻሊስቱ ዶክተር ውላታው ጫኔ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ÷ ሁለት አይነት የጉበት ካንሰር ሲኖር የመጀመሪያው መነሻው ከዛው ከጉበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሌላ የሰውነት አካል ተሰራጭቶ የመጣ የጉበት ካንሰር አይነት ነው፡፡

ይህም ማለት ለምሳሌ የአንጀት እንዲሁም የጨጓራና የጡት ካንሰር መሰራጨት ሲጀምሩ መጀመሪያ የሚያጠቃው ጉበትን ሲሆን ይህ ተሰራጭቶ የመጣ የጉበት ካንሰር እንደሚባል ይገልጻሉ፡፡

ከዛው ከጉበት የሚነሳ የጉበት ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች አንደኛው ማንኛውም የጉበት ጠባሳ የሚፈጥሩ ነገሮች ናቸው፤ ከእነዚህ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሱት ሄፒታይተስ ቢ እና ሄፒታይተስ ሲ መሆናቸውንም ነው የሚናገሩት፡፡

እነዚህ ያላቸው ሰዎች ጉበታቸው ላይ በቫይረሱ ምክንያት የሚመጣ ቁስለት ሲኖር ያ ቁስለት የጉበት ህዋሶችን ይጎዳል፤ እነዛ የጉበት ህዋሶች ደግሞ እራሳቸውን ለመተካት በሚሄዱበት ሂደት እድገቱ ወደ ካንሰርነት ሊቀየር የሚችል እብጠት ጉበት ላይ ሊፈጠር እንደሚችል አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ምግቦች ውስጥ ሊገኝ የሚችል አፍላ ቶክሲን (Aflatoxin) የተባለ የፈንገስ አይነትለጉበት ካንሰር አጋላጭ ሊሆን እንደሚችል ዶክተር ውላታው ይናገራሉ፡፡

አብዛኛው የጉበት ካንሰር ህመም ምልክት የላቸውም የሚሉት ዶክተር ውላታው ምልክት ማሳየት ከጀመሩ ግን ብዙዎቹ ደረጃው ከፍ ያለ ሲሆን ነው፡፡

በዚህም አይን ቢጫ መሆን ፣ ተደጋጋሚ ትውከትና ሌሎች ህመሞች ይታያሉ ነው ያሉት ዶክተር ውላታው፡፡

ክትባት መውሰድ፣ አመጋገብን ማስተካከል (ተብላልተው በሚወሰዱ ምግቦች ላይና ፈንገስ ሊይዙ የሚችሉ ምግቦች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ)፣ ቅባት ያለው ነገሮችን አለማብዛት፣የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ጉበቱ ላይ ጠባሳ እንዳለ ከታወቀ ችግሩ የገዘፈ እንዳይሆን ተገቢውን የህክምና ክትትል ማድረግ መከላከያ መንገዶቹ ናቸው፡፡

በጊዜ ከታወቀና ታማሚዎች ዘግይተው የማይመጡ ከሆነ እንደ ደረጃው የጉበት ካንሰር የመዳን እድል አለው ነው ያሉት ዶክተር ውላታው ፡፡

ህክምናውም እጢውን ከእነ ጉበቱ ነቅሎ ማውጣት እና የጉበት ንቅለ ተከላን እንደሚያካትትም ጠቁመዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.