Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ ያተኮረ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የባንኮች እና ኢንሹራንስ ተቋማት ሃላፊዎች እና የቦርድ አባላት የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ ላይ ያተኮረ መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱራህማን ኢድ ታሂርና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም መንግስት በኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የ25 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ እንደሚኖረው በሚጠበቀው በዚህ የሰነደ መዋዕለ ነዋይ ገበያ ለሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የባለቤትነት ድርሻ ለመሸጥ ስራ መጀመሩ ተጠቁሟል።
ገበያው የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ሚና እንደሚያሳድግ ገልጸው፣ ይህም ከ60 ዓመት በኋላ ዳገም የተጀመረ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የአክሲዮን እና የብድር ወይም ቦንድ ሰነደ መዋዕለ ነዋዮችን በሚቀጥለው ዓመት አስተማማኝና ቀልጣፋ በሆነ የዲጂታል የገበያ ስርዓት ለግዥ እና ሽያጭ የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ነዋይ ገበያ መንግስትን ጨምሮ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የገበያው የመስራች ባለአክሲዮኖች እንዲሆኑ የሚያስችለውን ስራ አጠናቆ፣ በዛሬው ዕለት በይፋ ወደ ድርሻ ሽያጭ ምዕራፍ መሸጋገሩ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ባቋቋመው የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አማካኝነት የገበያውን የቢዝነስ ፕላን እና የአዋጭነት ጥናት፣ የገበያ ቅርጽ፣ የአስተዳደር እና የግብይት ህጎች እና መመሪያዎች፣ የማዘጋጀት እና አስፈላጊ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የመለየት ስራዎች ተጠናቀዋል።
የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት፣ በተለይ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዚህ ታሪካዊ ገበያ የባለቤትነት ድርሻቸውን እንዲያጠናከሩ ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎች መመቻቸታቸውም ተገልጿል።
የሰነደ መዋዕለ ነዋይ ገበያ ምስረታ ሂደት አስተባባሪ ጥላሁን ካሳሁን (ዶ/ር) “በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፋይናንስ ገበያ ስርዓት ማቋቋም ለዜጎች፣ ለሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች፣ ለተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት የካፒታል ሰነድ ግዥና ሽያጭን የሚያመቻች ሲሆን÷ ለመንግስት፣ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች እዲሁም ለግል ኩባንያዎች የተጠናከረና የስጋት መሰረቱ የተሰበጣጠረ የብድር ገበያ መገልገያ አማራጮችን ያቀርባል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱራህማን ኢድ ታሂር የሰነደ መዋዕለ ነዋይ ገበያው የመንግስት ትልቅ የሪፎርም አካል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.