Fana: At a Speed of Life!

በአፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑክ ከተለያዩ የሩሲያ የመንግስት ተቋማት ጋር መከረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የተመራው ልዑክ ከተለያዩ የሩሲያ የመንግስት ተቋማት ጋር ተወያየ፡፡

የልዑካን ቡድኑ ከሩሲያ ተቋማት ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነቱን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል ነው የተባለው፡፡

ቡድኑ ከሩሲያው የማዕድን ሀብቶች ኤጀንሲና የሩሲያና ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የሳይንስና እና የቴክኒክ ትብብር የጋራ ኮሚሽን የሩሲያ ወገን ሊቀመንበር ፔትሮቭ ቆይታ አድርጓል፡፡

በቆይታውም ሁለቱ ሀገራት ሩሲያ ከፍተኛ ልምድ ካካበተችበት የማዕድን ዘርፍ ልምድ ማካፈል በሚቻልበት፣ የሩሲያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በሚደርጉበት እንዲሁም ኢትዮጵያ ከሩሲያ እያገኘች ያለችው የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡

ሊቀመንበር ፔትሮቭ ፥ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከር የሚያስችላትን ፍኖት ካርታ እያዘጋጀች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

በቅርቡም ከኢትዮጵያ ወገን ጋር በረቂቁ ላይ በመነጋገር ወደ ሥራ እንደሚገባ እና ከዚህ ጋር በተያያዘም በአዲስ አበባ የተከፈተው የሩሲያ የንግድ ተልዕኮ ወደ ሥራ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በተመሳሳይ አፈጉባኤ አገኘሁ ከሩሲያ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ግሩዝዴቭ አሌክሲ ጋርም ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም ፥ ኢትዮጵና ሩሲያ በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት በኢኮኖሚው ዘርፍም ለመድገም መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች በቀጥታ ወደ ሩሲያ ለማስገባት ያሉ ዕድሎችን ለማጥናትና፣ የወጪና የገቢ ምርቶችን ዓይነት ለማበራከትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ በጋራ ለመንቀሳቀስ መስማማታቸውም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ ከሩሲያ የንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ካትሪን ጋር ውይይት ማድረጉ ተገልጿል፡፡

በዚህም የሁለቱ ሀገራት የንግድ ም/ቤቶች ጠንካራ ትስስር በመፍጠር በኢትዮጵያና በሩሲያ ባሉ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

አፈ ጉባዔው ፥ በሩሲያ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋርም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በሩሲያ ፌዴሬሽን በቀጣይ በሚኖረው ቆይታ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት ጋር እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.