Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም 10 ቦምቦችን ደብቀው ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በማሰብ 10 ቦምቦችን በቤት ውስጥ ደብቀው ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ።

ሕገ -መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት የሽብር ወንጀል ለመፈፀም 10 ቦምቦችን በማምጣት በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በተከራዩበት መኖሪያ ቤት ቦምቦችን ደብቀው ተይዘዋል በተባሉት ተጠርጣሪዎች ላይ  ነው ምርመራ እንዲደረግባቸው የ14 ቀን ጊዜ የተፈቀደው።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት፥ የፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ያቀረበውን የሽብር ወንጀል የጥርጣሬ መነሻ ዝርዝር ነጥቦችን እና የተጠርጣሪዎችን መከራከሪያ ነጥብ ከሰዓት በኋላ በነበረ ቀጠሮ ተመልክቷል፡፡

የሽብር ተግባር ለመፈጸም 10 ቦምቦች ደብቀው ተይዘዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎቹ 1ኛ ሞላልኝ ሲሳይ እና 2ኛ አብርሃም ጌትነት ይባላሉ።

የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ተጠርጣሪዎቹ ህገመንግስቲዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ፣ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በማደራጀትና በመደራጀት በአማራ ክልል እንዲነሳ ባደረጉት የሁከትና ብጥብጥ የሽብር ወንጀል ተግባር በ29 ሰዎች ላይ የሞት በ54 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን እንዱሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሶ የጥርጣሬ መነሻውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።

በአማራ ክልል የተፈጸመውን የወንጀል ተግባር በተመሳሳይ ለመፈፀም 10 ቦምቦችን አምጥተው በየካ ክፍለ ከተማ በተከራዩበት መኖሪያ ቤት ደብቀው እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን መርማሪ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ገልጿል።

ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ ማስረጃዎችን ሰብስቦ ለመቅረብ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠውም ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ በበኩላቸው፥ ተጠርጣሪዎች በጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት እና  ሁከትና ብጥብጥ ማስነሳት ወንጀል በሌላ ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ምርመራ ሲከናወንባቸው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም በሌላ የሽብር ወንጀል መዝገብ ዛሬ ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁ አግባብ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል።

ጠበቃቸው የደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸውም ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ፥  ከዚህ በፊት በተጀመረባቸው የምርመራ ስራ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የሚያመላክት ማስረጃ ማግኘቱን ጠቁሞ በተገኘ መነሻ ማስረጃ መሰረት በሽብር ወንጀል መዝገብ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረጉን አብራርቷል።

ተጨማሪ ጊዜ አያስፈልግም ተብሎ ለተነሳ መከራከሪያ ነጥብ ምላሽ የሰጠው መርማሪ ፖሊስ፥ የቀሪ ምስክሮችን ቃልና በተለያዩ ባንኮች የተደረገውን የገንዘብ  ዝውውር ተጨማሪ የቴክኒክ ማስረጃዎችን ለማምጣት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጾ ተከራክሯል።

በዋስ ቢወጡ በተመሳሳይ የሽብር ተግባር ሊፈጽሙና ቀሪ ማስረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ በማለት ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ ምርመራ ማከናወን አስፈላጊ ነው ሲል የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

የምርመራ ውጤቱት ለመጠባበቅ ለግንቦት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.