Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ኮሎምቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ኮሎምቢያ በፖለቲካ ምክክርና በሌሎች የትብብር መስኮች በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

አገራቱ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር መስማማታቸውንም አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ከገቡት የኮሎምቢያ ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍራንሲያ ኢሌናን ጋር ተወያይተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅትም÷ ኮሎምቢያ ከ50 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ዳግም ለመክፈት በመወሰኗ አድናቆታቸውን ገልፀውላቸዋል።

ሁለቱ አገራት በዓለም አቀፍ መድረኮች ተመሳሳይ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን አስታውሰው÷ ኢትዮጵያ በቀጣይ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም፣ በአቪዬሽን እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ከኮሎምቢያ ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን÷ኮሎምቢያ በቀጣይ ዓመታት በተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተዘዋዋሪ አባል ቦታ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረቧንም አስታውሰዋል፡፡

ይህም አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጣናዊ እና ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ይበልጥ በትብብር እንዲሰሩ ያግዛል ነው ያሉት።

ምክትል ፕሬዚዳንቷ በበኩላቸው÷ ኮሎምቢያ ዳግም በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ለመክፈቷ አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በቀጣናው ያላት ጠንካራ ተፅዕኖ  እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ውሳኔውም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ መሆኑን ጠቅሰው÷ በቀጣይም ኮሎምቢያ በቀጣናዊና አህጉራዊ፣ እንዲሁም በባለብዙ መድረኮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

ኮሎምቢያ በዓለም መድረክ የምትታወቅበትን የቡና ልማት ቴክኖሎጂ መልካም ተሞክሮ  ለኢትዮጵያ እንደምታጋራም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያና ኮሎምቢያ ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት በፈረንጆቹ 1947 ሲሆን÷ አገሪቱ በ1967 በአዲስ አበባ የከፈተችውን ኤምባሲ በፈረንጆቹ 1974 መዝጋቷ ይታወሳል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.