Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል የመሪዎች ኮንፈረንስ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ በትኩረት እየመከረ ነው- አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል የመሪዎች ኮንፈረንስ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየመከረ መሆኑን የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ዛሬ የተጀመረውን አማራ ክልል የከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ኮንፈረስ ውሎ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም÷ ኮንፈረንሱ ክልላዊ ሁኔታውን የሚገልጽ፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታው አልጋ በአልጋ እንዳልመጣ የሚያስታውስ፣ የተገኙ ድሎች ሁሉ ያለፈተና እንዳልተገኙ የዳሰሰ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በፈተናዎች ባለመንበርከክ፣ በፈተናዎች እየፀኑ፣ ፈተናዎችን ወደ እድልና ድል እየቀየሩ ለተሻለ ድል መዘጋጀት እንደሚገባ መነሳቱንም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ይፈልጋል ያሉት ኃላፊው÷ ሕዝቡ በሚፈልገው መልኩ መምራት እንዲቻል የሚያስችል አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ አሁናዊ ፈተናዎች ምንድን ናቸው፣ ምን አይነት መልካም ነገሮች አሉ፣ ፈተናዎችን እንዴት አድርገን ወደ ድል እንቀይራለን የሚለው በስፋት እየተነሳ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ከኢትዮጵያዊነት ልዕልና ላይ መሠረት ያደረገ ትግል አስፈላጊ እንደሆነ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

መሪዎች ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታውን ተገንዝበው ለወቅቱ የሚመጥን ጽናት፣ ቁርጠኝነት እና ለመስዋዕትነት ዝግጁ መሆን እንደሚያሻ በኮንፈረሱ ውይይት እየተደረገበት ነው ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ተረጋግቶ ዋነኛ ጥያቄዎች ላይ አተኩሮ እንዲሠራ የፖለቲካ ሥነ ምህዳር መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የአማራን ሕዝብ ጥያቄ እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያለመረዳት ችግሮች መኖራቸውንም ያነሱት ኃላፊው÷ ኮንፈረንሱ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል መግለጻቸውንም አሚኮ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.