Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ከጄጁ ደሴት አስተዳደር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ከጄጁ ደሴት አስተዳደር ኦ ያንግ ሁን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው በኢትዮጵያ እና በጄጁ ደሴት በቱሪዝም፣ በባህል እንዲሁም ባህላዊ ቅርሶች እና የተፈጥሮ መስህቦች ዙሪያ በትብብር መስራት በሚቻልበት አግባብ ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በዚህ ወቅት አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለውን ልዩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አስታውሰው፥ ኢትዮጵያ አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ጋር ለማገናኘት እንደ መግቢያ ሆና እንደምታገለግልም ተናግረዋል።

አያይዘውም የኢትዮጵያን የብሄረሰቦች ብዝሃነት፣ የብዝሃ ህይወት እና በተመድ የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች እንዳሏት አውስተዋል።

እነዚህ ምክንያቶች ኢትዮጵያን ምቹ የጎብኚ መዳረሻ ለማድረግ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በመጥቀስም፥ በጎብኚዎች ከሚዘወተረው የጀጁ ደሴት ጋር ያለውን ተመሳሳይነትም አንስተዋል።

አምባሳደሩ አክለውም በኢትዮጵያ ከተሞች ወይም ክልሎች እና በጄጁ ደሴት መካከል በተለይም ቱሪዝም ዘርፍ ትብብር መፍጠር የጋራ ጥቅም እንደሚያስገኝ አስረድተዋል።

አስተዳደሩ በጄጁ ደሴት እና በኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ግንኙነት መፍጠር የሚቻልበትን ሁኔታ እንደሚያጤኑም አስገንዝበዋል።

የጄጁ አስተዳደር ኦ ያንግ ሁን በበኩላቸው በኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ያለውን ልዩ ታሪካዊ ግንኙነት እውቅና እንደሚሰጡ ገልፀዋል።

የአምባሳደሩን ጉብኝት ያደነቁት አስተዳደሩ በኢኮኖሚ ልማት፣ በቱሪዝም እና ባህል ግንኙነትን ማጠናከር ያለውን ጠቀሜታ ገልጸውላቸዋል።

አክለውም “በ ጄጁ ደሴት እና አዲስ አበባ መካከል የሚደረገውን የልምድ ልውውጥ እና ትብብር ተግባራዊነት እንደሚያጤኑትም ነው የገለጹት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.