Fana: At a Speed of Life!

መስከረም አበራን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች ላይ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የ7 ቀን ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መስከረም አበራን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የ7 ቀን ጊዜ ተፈቀደ።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን ጊዜ ውስጥ የሰራውን እና ቀረኝ ያላቸውን የምርመራ ስራዎች እንዲሁም የተጠርጣሪዎችን የመከራከሪያ ነጥቦች መርምሮ ነው የምርመራ ማጠናቀቂያ የ7 ቀን ጊዜ የፈቀደው።

ተጠርጣሪዎቹ መስከረም አበራ፣ ሳሮን ቀባው፣ ዮርዳኖስ አለሜ፣ ቢሰጥ ተረፈ፣ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) እና ታደለ መንግስቱ ትናንት በነበራቸው ቀጠሮ ከአምስት ጠበቆቻቸው ጋር ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ ከ15 ባንኮች ማስረጃ ማምጣቱን፣ የተጠርጣሪዎችን የጣት አሻራ ማስነሳቱን፣ የኋላ ታሪካቸውን የመለየት ስራ መስራቱን፣ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 27/2 መሰረት የተከሳሽነት ቃላቸውን መቀበሉን፣ የቴክኒክና የፎረንሲክ ማስረጃዎችን በከፊል ማስመጣቱን እና በተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት ብርበራ ማድረጉን ገልጿል።

ቀሪ ያላቸውን ስራዎች ማለትም በወንጀለኛ መቅጫ ስነ/ህግ ቁጥር 30 መሰረት የቀሪ የምስክር ቃል መቀበል፣ ከቀሪ ባንኮችና ከተለያዩ ተቋማት ማስረጃዎችን ማስመጣት ፣ በአማራ ክልል በተፈጸመ የሁከትና አመፅ ማስነሳት ተግባር ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ውጤት ከፌደራልና ከክልል ተቋማት ማስመጣት ፣ ግብረዓበር ተከታትሎ የመያዝ ስራ እንደሚቀረው ጠቅሶ በወ/መ/ስነ/ህግ ቁጥር 59/2 መሰረት ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ከሀገር ሊሸሹ ይችላሉ ሲል ግምታዊ ስጋቱን ገልጾ የዋስ መብታቸው እንዳይፈቀድም ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ውስጥ ዕድገት ያለው ምርመራ አላደረገም ሲሉ ተከራክረዋል።

ቀሪ ስራ ተብሎ የቀረበው ምክንያቶች ለተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ሆነው መቅረባቸው ተገቢነት የለውም ሲሉ ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች በእስር በቆዩባቸው ጊዜያቶች የተሳትፎ ድርሻቸው ተለይቶ አልቀረበም፣ ደንበኞቻችን በዋስ ቢወጡ የሚፈጥሩት መሰናክል ስለመኖሩ በፖሊስ ባልተገለፀበት ሁኔታ ላይ ደንበኞቻችን በእስር የሚቆዩበት ምክንያት የለም በማለት ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የዋስትና መብት እንዲፈቀድ የጠየቁ ሲሆን÷ በተጨማሪም ምንም ምስክር አልቀረበም ሲሉም ተከራክረዋል።

ዮርዳኖስ የተባለው ተጠርጣሪና መስከረም አበራ በሙያቸው እንደሚሰሩና ለእስር የሚዳርግ ድርጊት አልፈፀምንም ብለው ተከራክረዋል።

ፖሊስ በበኩሉ ማንም ሰው ያለምክንያት በቁጥጥር ስር እንደማይውልና የወንጀል ተሳትፎ የመነሻ ጥርጣሬ ሲኖር ብቻ ወደ ህግ እንደሚቀርብ አስረድቷል።

የተጠርጣሪዎቹ ተሳትፎ ተለይቶ አልቀረበም ለሚለው የጠበቆች የመከራከሪያ ነጥብን በሚመለከት ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ የፖለቲካና ፣ የወታደራዊና የሚዲያ ክንፍ በማዋቀር በህቡዕ በመደራጀት የተደረገ የሽብር ወንጀል ተግባር እንቅስቃሴ መኖሩን የሚያመላክት ማስረጃ ሰብስበናል ሲል መልስ ሰጥቷል።

በዚህ መልኩ መርተው በቀሰቀሱት አመፅና ብጥብጥ ምክንያት ከ18 ሰው በላይ ህይወት መጥፋቱን፣ ከ46 የሚበልጡ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን እና በሚሊየኖች የሚቆጠር ንብረት ላይ ጉዳት ተከስቷል ሲል ፖሊስ በሰጠው ምላሽ አብራርቷል።

በተጨማሪም መርማሪው ከተጠርጣሪዎች መካከል አንድ ተጠርጣሪ በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች የሽብር ወንጀል ጥቃት እንዲፈጸም በማቀድ 10 ቦምቦችን ከአማራ ክልል በማምጣት ለሌሎች ተጠርጣሪዎች መስጠቱን ተከትሎ ቦምቦቹ ሳይፈነዱ መያዛቸውን መርማሪ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ገልጿል።

ተጠርጣሪዎች አይተዋወቁም በማለት ጠበቆች በሰጡት አስተያየት ላይ መልስ የሰጠው ፖሊስ በህቡዕ በመደራጀት እንቅስቃሴ ተደርጓል ሲል ገልጿል።

በተለይም ጠበቆች ደንበኞቻችንን በሚመለከት ምንም ምስክር ቃል አልተቀበለም በማለት ያነሱትን መከራከሪያ ነጥብን በሚመለከት ፖሊስ ተጠርጣሪዎች በተጠረጠሩበት ወንጀል ከ20 በላይ የምስክር ቃል መቀበሉን የፎረንሲክ ማስረጃ መሰብሰቡን ፖሊስ ገልጾ መልስ ሰጥቷል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ መርምሮ ተጨማሪ ጊዜ መሰጠት አለበት ወይስ የለበትም የሚለውን ለመወሰን በይደር ለዛሬ በያዘው ቀጠሮ መሰረት የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ፖሊስ የቀረውን የምርመራ ስራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የ 7 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.