Fana: At a Speed of Life!

መከላከያን በሳይበር የውጊያ ዘርፍ ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የዘመናችን አንዱ የውጊያ መስክ በሆነው በሳይበር ዘርፍ መከላከያን በሰው ሀይልና በቴክኖሎጂ የማብቃቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጹ።

 

“የሳይበር ደህንነት የጋራ ሀላፊነት ነው” በሚል መሪ ቃል የመከላከያ የሳይበር ዋና ዳይሬክቶሬት የተመሰረተበትን አንደኛ አመት አክብሯል።

 

በመከላከያ የአስር አመት የሰራዊቱ የግንባታ ዕቅድ ውስጥ በቴክኖሎጂና በሰው ሀይል የተደራጀ የሳይበር ሀይል ለመገንባት የተጀመረው ስራ አበረታች መሆኑን የጠቀሱት ኤታማዦር ሹሙ የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

 

የመከላከያ የሳይበር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ደረጄ ደመቀ፥ ክፍሉ ከተቋቋመ ጀምሮ በመንግስትና በተቋም ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችንና ወንጀሎችን ለመከላከል አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

 

ለሰራዊቱ አመራሮችና አባላት ግንዛቤ በመስጠትና ተቋማዊ የሳይበር ደህንነት መነቃቃትን ለመፍጠር የተሰሩት ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

 

በቀጣይም የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሳይበር ትንተና እና የቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት ወሳኝ ሀገራዊ ሀብቶችን ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሳይበር ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ መቅረፅና መተግበር፣ የህግ ማዕቀፎች፣ መለኪያዎች እና መመሪያዎች እንዲኖሩ ለማድረግ  የተጀመሩት ስራዎች በታቀደላቸው ጊዜ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

በዕለቱ የመከላከያ ሳይበር ዋና ዳይሬክቶሬት አዲስ መለያ ዓርማ የተመረቀ ሲሆን ክፍሉ ለደረሰበት ደረጃ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት የክፍሉ መለያ ዓርማ በሽልማት እንደተበረከተላቸው የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.