Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ አጋር ሀገራት ተዋጊ ጀቶችን ለዩክሬን ቢያቀርቡ እንደምትፈቅድ አስታወቀች

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ አጋር ሀገራት አሜሪካ ሰራሽ ተዋጊ ጀቶችን ለዩክሬን ቢያቀርቡ እንደምትፈቅድ አስታወቀች።

 

የዋሺንግተን የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በጃፓኑ የቡድኑ ሰባት አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ “አጋር ሀገራት ለዩክሬን ተዋጊ ጄቶችን ማቅረብ ከፈለጉ አሜሪካ እንቅፋት አትሆንባችሁም” ማለታቸውን ገልጸዋል።

 

ከዚህ ቀደም አሜሪካ ሀገራት አሜሪካ ሰራሽ የሆኑትን ዘመናዊ ኤፍ 16 ተዋጊ የጦር ጄቶች ለዩክሬን እንዳያቀርቡ መከልከሏ ይታወሳል።

 

ክልከላው የባይደን አስተዳደር አጋር ላላቸው ሀገራት የሸጣቸው ተዋጊ ጄቶች ከሀገራቱ ለዩክሬን እንዳይሸጡ አልያም በድጋፍ መልክ እንዳይቀርቡ የሚያደርግ ነበር።

 

አሁን ላይ ይህ ውሳኔ የተቀለበሰ ሲሆን፥ የአሜሪካ ተዋጊ ጄት አብራሪዎችም ለዩክሬን አቻወቻቸው የስልጠና ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሏል።

 

የብሄራዊ ደህነነት አማካሪውም ዋሺንግተን በቀጣዮቹ ወራት ተዋጊ ጄቶቹ ለዩክሬን በሚቀርቡበት አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ከአጋሮቿ ጋር ትመክራለች ማለታቸውን አር ቲ እና ቢ ቢ ሲ ምንጮችን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።

 

ዩክሬን ምዕባውያን ሀገራት ዘመናዊ የጦር ጄቶች እንዲያበረክቱላት ፅኑ ፍላጎት የነበራት ሲሆን፥ የአሁኑን የዋሺንግተን እርምጃም “ታሪካዊ ውሳኔ” ስትል አሞካሽታዋለች።

 

የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪም ተዋጊ ጄቶቹ የዩክሬንን ጦር የአየር ላይ ብቃት ያጠናክሩታል ብለዋል።

 

በአንጻሩ ሞስኮ ምዕራባውያን ለኪየቭ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከማቅረብ እነዲታቀቡ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።

 

ክሬሚሊንም ይህ የምዕራባውያን አካሄድ ምናልባትም “ጦርነቱን ከማራዘምና ወታደራዊ ዘመቻው ላይ ትንሽ ተግዳሮት ከመፍጠር የዘለለ ፋይዳ የለውም” ሲል መግለጹ አይዘነጋም።

 

አሁን ላይ አሜሪካ እና አጋሮቿ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ በግጭቱ በቀጥታ ተሳታፊ መሆናቸውን ያመላክታልም ብላለች ሩሲያ።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.