Fana: At a Speed of Life!

የ”ሿሿ ” ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ መቀጠሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተለምዶ ሿሿ የሚባለውን ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራውን መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀሉን ለመከላከል እና ወንጀለኞቹን ህግ ፊት ለማቅረብ በጥናት ላይ ተመስርቶ ባከናወነው ተግባር ነው በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ወንጀሉን ሲፈፅሙ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ አያጣራ የሚገኘው፡፡

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ግለሰቦች በቦሌ ክፍለ ከተማ ስድስት ቦታዎች ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ሶስት ቦታዎች እንዲሁም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሶስት ቦታዎች ላይ ወንጀሉን መፈፀማቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳትፎ ያላቸው 19 ወንዶችና 6 ሴቶች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን÷ ሁለት አነስተኛ ህዝብ ማመላለሻ  መኪናዎች እንዲሁም ግለሰቦቹ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚጠቀሙባቸው 4 ልዩ ልዩ ተሸከርካሪዎች ፣ 82 ሺህ 680  ጥሬ ብር ፣ 14 ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ስማርት ስልኮች እና የቀን ተቀማጭ የሚያስቀምጡበት ደብተር በኤግዚቢትነት እንደተያዘ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ ፋንታ አስረድተዋል፡፡

ግለሰቦች ምንም አይነት ህጋዊ ገቢ የሚያገኙበት ስራ የሌላቸው ቢሆንም ከፍተኛው በቀን 35 ሺህ ብር አነስተኛው 5ሺህ ብር የቀን ተቀመጭ ሲያደርጉ እንደነበር  በኤግዚቢትነት ከተያዘው ሰነድ ማረጋገጥ መቻሉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ ስፍራዎች ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የተፈፀመባቸው ግለቦች አዲስ አበባ ፖሊስ  ጉለሌ ክፍለ በመቅረብ በኤግዚቢትነት ከተያዙ ስልኮች መካከል መምረጥ እንደሚችሉ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.