Fana: At a Speed of Life!

የዓረብ ሊግ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያወጣው መግለጫ በግብፅ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የተጠለፈ ነው -ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) የዓረብ ሊግ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያወጣው መግለጫ ተቀባይነት የሌለውና በግብፅ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የተጠለፈ ነው ሲሉ ምሁራን ገለፁ።

የግድቡን ሁኔታና የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ተመራማሪ  አደም ካሚል (ረ/ፕ/ር )÷ መሰል እውነታን ያደበዘዙ ጩኸቶች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሙሌት በተቃረበ ቁጥር የተለመዱና እውነታውን ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ናቸው ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አማቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ሴኔሳ ደምሱ በበኩላቸው ÷የአሁኑ የዓረብ ሊግ መግለጫ የግብጽ ውሸትን በማለማመድ እውነት ለማድረግ የመሞከር ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የዓረብ ሊግ መግለጫ እውነትን ያልተከተለ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያላከበረና አድሎ ያለበት መሆኑን ነው ምሁራኑ ያመላከቱት፡፡

ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ እውነት ቢኖራትም እንኳ እውነታዋን በተከታታይ የዲፕሎማሲ ስራዎች በመስራት ለተቀረው ዓለም ማሳወቅ  እንደሚገባትም ምሁራኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ዓረብኛ ቋንቋን ጨምሮ ሌሎች ቋንቋዎችን በመጠቀም እውነታውን የሚያስረዱ የዲፕሎማሲ መንገዶችን መከተል፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲን ማዳበር፣ ከአጀንዳ ተቀባይነት በመውጣት ወደ አጀንዳ ሰጭነት መሻገር  ይገባል ብለዋል፡፡

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.