Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የበለጸገች አፍሪካን ለመፍጠር የምታበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክራ ትቀጥላለች – አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያም የበለጸገችና አንድነቷ የተጠናከረች አፍሪካን ለመፍጠር የምታበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች፣ የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የፓናል ውይይቱ እየተካሄደ ነው።

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በዚሁ ጊዜ ÷ በአፍሪካ አንድነትን ለማጠናከርና የምጣኔ ኃብት እድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል።

በተለይም ምጣኔ ኃብታዊ ውህደትና ትስስር ለማረጋገጥ በጅምር ላይ ያለው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናን ትግበራ ማፋጠን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አፍሪካ ያላት የተፈጥሮ ኃብትና አምራች የሰው ኃይል ለዕድገቷ እድል መሆናቸውን አንሰተው ፥ እነዚህን ኃብቶች በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

የአህጉሪቷን እድገት ወደኋላ የሚጎትቱ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀትም አፍሪካዊ መፍትሄ ለአፍሪካዊ ችግር መርህን ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፓን አፍሪካን ጽንሰ ኃሳብ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አምባሳደር ምስጋኑ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያም የበለጸገችና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን ለመፍጠር የምታበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክራ እንደምትቀጥል ሚኒስትር ዴኤታው አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.