Fana: At a Speed of Life!

ከ20 በላይ ኩባንያዎች ወደ ግል በሚዞሩ ስኳር ፋብሪካዎች ጨረታ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት አሳዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ20 በላይ ኩባንያዎች ወደ ግል እንዲዛወሩ ጨረታ የወጣባቸውን የስኳር ፋብሪካዎች ለመግዛት ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለፀ፡፡

በመንግስት ባለቤትነት የተያዙ 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግሉ ለማዞር መንግስት እ.ኤ.አ. ነሐሴ 2022 ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

በዚህም በመንግስት ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዛወር የታሰቡት የስኳር ፋብሪካዎች አርጆ ዴዴሳ፣ ከሰም፣ ኦሞ ኩራዝ 1፣ ኦሞ ኩራዝ 2፣ ኦሞ ኩራዝ 3፣ ኦሞ ኩራዝ 5፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ ናቸው።

ይህን ተከትሎም ከ20 በላይ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መንግስት ባወጣው ጨረታ ላይ ለማሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸው ተገልጿል።

በዚህም የመንግስት ማሻሻያዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የጨረታ ማስረከቢያውን ሂደት የሚገልጽ አጠቃላይ የጨረታ ሰነድ ወጥቷል።

የፕራይቬታይዜሽን ወሰን፣ ለተጫራቾች የሚያስፈልጉ መስፈርቶች፣ የግምገማ መስፈርቶች እና የሂደቱ የጊዜ ሰሌዳን ጨምሮ ስለ ግብይቱ ዝርዝር መረጃ በጨረታ ሰነዱ ላይ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡

በዚህም ፍላጎት ላሳዩት ተጫራቾች ምስጋና ያቀረበው መንግስት ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉና ፕሮፖዛላቸውን እንዲያስገቡ ጠይቋል፡፡

እነዚህ የስኳር ፋብሪካዎች በተሳካ ሁኔታ ወደ ግል እንዲዘዋወሩ መደረጉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በላይ በሀገሪቱ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ያስችላል ተብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.