Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀረጥ ነጻ የሚሸጡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ ነው – አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሽያጭ ማዕከል ከቀረጥ ነጻ የሚሸጡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች አበረታች ውጤት እያመጡ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

አቶ መላኩ አለበል ከአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ጋር በአየር መንገዱ ከቀረጥ ነጻ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የሽያጭ ማዕከል እንቅስቀሴ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ÷ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች የቀረጥ ነፃ የሽያጭ ማዕከል አፈጻጸም፣ የቆዳና ምርቶችን ከማስተዋወቅ፣ የምርት ጥራትና ተደራሽነትን ከማስፋፋት፣ ከውጪ ወደሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት በሚቻልበትና የውጭ ምንዛሬ የገቢ መጠን ማሳደግ ላይ መክረዋል፡፡

የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የቀረጥ ነጻ የንግድ ማዕከል ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ በምርት ጥራት፣ በገቢ እድገት፣ የመዳረሻ ገበያ ከማሰደግ እና ለዜጎች ተጨማሪ የስራ እድልን በመፍጠር ረገድ አስተዋጽኦ እንዳለውና አበረታች ውጤት እያመጣ መሆኑን አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የቆዳ ኢንዱስትሪው ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ ከተሰሩ ስራዎች አንዱ የሆነው የሽያጭ ማዕከሉ ወደ እንቅስቃሴ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በተቋም ደረጃ እስፈላጊውን ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የታየውን አበረታች ውጤት ተከትሎም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በዘርፉ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች ተጨማሪ የማምረቻ ቦታዎች የማመቻቸት ስራ መሰራቱንም አንስተዋል፡፡

ከቆዳናቆዳ ውጤቶች በተጨማሪም ሌሎች የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገቡ የማድረግ  ስራ ለመስራት ከአየር መንገዱ ጋር ከስምምነት መድረሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.