Fana: At a Speed of Life!

“ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያገኘነውን ት/ት በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን የመከላከልና ጠንካራ ምላሽ የመስጠት አቅምን መገንባት ላይ ማዋል ይገባል”- ዶ/ር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያገኘነውን ትምህርት በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን የመከላከል፣ ፈጥኖ የመለየትና ጠንካራ ምላሽ የመስጠት አቅምን መገንባት ላይ ማዋል ይገባል” ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው 76ኛው የዓለም ጤና ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ÷ኢትዮዽያ የዓለም ጤና ድርጅት መስራች ሀገሮች አንዷ መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡

በፈረንጆቹ በ1956 የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ስምምነት መፈጸሙን አስተውሰው÷ ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ በተለይም የህብረተሰብ ጤና ክብካቤ ላይ ውጤት መመዝገቡን ገለጸዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣንና በታይላንድ ጤና ሚኒስቴር ሜድካል ሳይንስ ዲፓርትመንት መካከል የጋራ የትብብር መግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል።

በ76ኛው የዓለም ጤና ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የኢትዮጵያ ምግብና መድሐኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ እና የታይላንድ ጤና ሚኒስቴር ሜዲካል ሳይንስ ዲፓርትመንት ዋና ዳይሬክተር ሱፓክስ ሰሪላክ የጋራ ትብብር ሰነዱን ፈርመዋል፡፡

ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የላቦራቶሪ የጥራት ምርመራ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.