Fana: At a Speed of Life!

የግብርና እና ሌሎች ምርቶችን እንደ አዕምሯዊ ንብረት መጠበቅ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርናን ጨምሮ ሌሎች ልዩ ልዩ ምርቶች እንደ አዕምሯዊ ንብረት የሚጠበቁበትን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት የሚያስችል ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ ሆኗል።

ለሶስት ዓመት የሚተገበረው ፕሮጀክት ወጪ በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ እንደሚሸፈን ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ÷ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ያሏትን ታዋቂ የግብርና ምርቶች በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ከሕግ ማዕቀፉም ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች አንዱና ዋንኛ የሆነው የቡና ምርት ላይ የተለየ ትኩረት መሰጠቱን አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የማህበረሰብ ዕውቀት መሪ ስራ አስፈፃሚ ታደሰ ወርቁ በበኩላቸው÷ የሕግ ማዕቀፉን የያዘው ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ውስጥ በቦታ ስም ለሚገለጹ ምርቶች አዕምሯዊ መብት ጥበቃ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ መልከአ ምድርን የሚያመላክት የሕግ ማዕቀፍና የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም አዋጅና ደንብ በማዘጋጀት የንግድ ምልክቶችን ባለቤትነት ለማስጠበቅ ከተሞከሩ ሂደቶች በተጨማሪ በቦታ ጥራታቸው የሚጠቀሱ ልዩ ልዩ ምርቶችን እንደ አዕምሯዊ ንብረት የሚጠበቁበትን ስርዓት ለመፍጠር ፕሮጀክቱ ወሳኝ ጠቃሜታ አለው ነው ያሉት።

በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን በማየትም የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለማከናወንና የምርቶች መጭበርበር ተከስቶ ተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እንደሚያስችል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.