Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ አስር ቀናት የዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ አስር ቀናት የዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በቀጣዩቹ ቀናት በተለይም በሀገሪቱ በምዕራብ አጋማሽ የዝናቡ ሁኔታው ቀጣይነት ይኖረዋል ብሏል።

በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተስፋፋ ዝናብ የሚኖር  መሆኑን ያመላከተው ኤጀንሲው÷በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች እርጥበታማ የአየር ሁኔታ እየተጠናከረ እንደሚሄድ አመልከቷል።

የሚኖረው እርጥበትም ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍጎት መሟላት የሚጠቅም ሲሆን ለአርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግጦሽና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትም የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመልክቷል።

በሀገሪቱ የምዕራብ አጋማሽ እየተስፋፋ የሚሔደው ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታ ቀደም ብለው የመኸር እርሻ እንቅስቃሴን ለጀመሩ አካባቢዎችም ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቋል።

የእርጥበቱ ሁኔታ በተለይም የረጅም ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራትና አስፈላጊ ዝግጅት ለማድረግም መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎችም በባድ ዝናብ ቅጽበታዊ ጎረፍ ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግ ኤጅንሲው ጥሪ ማቅረቡን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.