Fana: At a Speed of Life!

የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሞስኮ ትምህርት ቤቶች ከመስከረም ጀምሮ ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 16 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞስኮ ትምህርት ቤቶች ከመስከረም ጀምሮ አማርኛ ቋንቋ ማስተማር ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የስፑትኒክ አለም አቀፍ የዜና አገልግሎት ድርጅት እና ሬዲዮ÷ በሩሲያ – አፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር ተስፋዎች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

ውይይቱ በአሌክሳንደር ጎርቻኮቭ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ፈንድ እና በሰብአዊ እርዳታ ማእከል ድጋፍ የተዘጋጀ ሲሆን÷ በሩሲያ እና በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ሀገራት መካከል አዲስ የትብብር አድማስ” ለመፍጠር ያለመ የባለሙያዎች እና ትምህርታዊ ዝግጅት አካል መሆኑ ተጠቁሟል።

በውይይቱ ላይ ከሩሲያ እና አፍሪካ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ የታሪክ ተመራማሪ ምሁራንና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የእስያ እና አፍሪካ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አሌክሲ ማስሎቭ ከፈረንጆቹ መስከረም 2023 ጀምሮ ቢያንስ አራት የሞስኮ ትምህርት ቤቶች ለህጻናት የአማርኛ እና የስዋሂሊ ቋንቋ ማስተማር እንደሚጀምሩ ይፋ አድርገዋል።

ማስሎቭ አክለውም በአዲሱ ልዩ መርሐ-ግብር በሞስኮ ትምህርት ቤቶች ዮሩባ ቋንቋን የሚያስተምሩበትን ዕድልም እየተመቻቸ መሆኑን ነው የገለፁት።

ወደ አፍሪካ በፍጥነት ፊትን ለማዞር ከኢኮኖሚው ጋር በቀጥታ ሊሰሩ የሚችሉ ፍጹም የተለዩ ባለሙያዎችን ማፍራት ያስፈልጋል ሲሉም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ አንድ ትልቅ አህጉር ብቻ ሳትሆን የተለያዩ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት እና ህብረ ብሔራዊ ማንነቶች ያሉባት አህጉር መሆኗን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡

ሩሲያ የአፍሪካ ልሂቃን ዲግሪ ለማግኘት ከሚሄዱባቸው አገሮች አንዷ እንደነበረች ያነሱት በውይይቱ የተሳተፉት ምሁር ቱንዴ አጂሌዬ÷አሁን ላይ ሩሲያ እና አፍሪካ የትምህርት ልውውጡን መቀጠል አለባቸው ሲሉ አክለዋል።

እንደ ምሁሩ ገለጻ በግብርና፣ በኃይል እና ኢንቨስትመንት ላይ ያለውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑንም አፅንዖት በመስጠት ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.