Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአፍሪካ መሪዎች አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ ቀንን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
በመልዕክታቸውም÷ የአፍሪካ መሪዎች በቀደምት አባቶች የተጀመረውን አንድነት ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከ60 ዓመት በፊት በዛሬዋ ቀን አዲስ አበባ የአፍሪካ አህጉርን የወደ ፊት አካሄድ የሚወስን ክስተት ማስተናገዷን አንስተዋል፡፡
 
በወቅቱ ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡ 32 ሀገራት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በአዲስ አበባ መመስረታቸውን ነው ያስታወሱት፡፡
 
በዚህ የመጀመሪያው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት÷ዛሬ በዓለም ፊት አንድነታችን ለማጠናከር በጋራ ቆመናል ማለታቸውን አንስተዋል፡፡
 
አሁን ላይ ከ60 ዓመታት በኋላ አፍሪካ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ሰዎችን በማስመዝገብ ከዓለም በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ አህጉር መሆኗንም አውስተዋል፡፡
 
ዛሬ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ጠንካራ ሆነው በዓለም አቀፍ መድረክ ወሳኝ ድምጽ እየሆኑ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ ለአህጉሪቱ እና ለህዝቦች በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ አፍሪካዊ የጋራ አቋምን በማስተዋወቅ እና ለአፍሪካ በመቆም ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዘናል ብለዋል።
 
ሆኖም የአባቶቻችንና የእኛ ምኞት የሆነውንን አጀንዳ 2063 ዕውን ለማድረግ ገና ብዙ ይቀራል ያሉ ሲሆን ፥ በተለይም አንድነትና ነፃነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች አባቶች ከምሥረታው በፊት ያወጁት እና ከዚያ በኋላም ትኩረት ያደረጉበት የጋራ ጉዳይ ነበር ብለዋል።
 
ከ60 ዓመታት በፊት የነበረው የዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረትን ተከትሎ መቀየሩንም ነው የገለጹት፡፡
 
ዛሬ እራሳችንን የምናገኝበት ውስብስብ ዓለም እና የእኛ የአፍሪካውያን ምኞት አንድነታችን ላይ ይበልጥ እንድናተኩር የሚያደርግ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡
 
“ህዝባችን አሁንም በድህነት ውስጥ እያለና ስርዓታችን በሙስና እና ግዴለሽነት ሲታመስ ነፃ መሆናችንን ማወጅ እንችላለን ወይ? ከተጋረጡብን ፈተናዎች ለማዳን ከራሳችን እና ከአህጉራችን አልፈን እየፈለግን ነፃነትን ማረጋገጥስ? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
 
ሀገራችንን እና አህጉራችንን ወደ ብልጽግና ለማምጣት የሚያስችል ሰፊ የሆነ የተፈጥሮ እና የቁሳቁስ ሃብት እንዳላቸው የማይካድ ሀቅ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ።
 
ሙስናን በመዋጋት፣ አህጉራችንን ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንቶች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እና የሕዝባችንን እምቅ አቅም አውጥተን በመጠቀም የምንፈልጋትን አፍሪካ መፍጠር አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
 
አፍሪካ ራሷን መመገብ እንደምትችል እና በተፈጠሮ ፀጋ በታደለችው አፍሪካ የወጣቶችን የምርት አቅም እና ፈጠራ በግብርና፣ኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎቸ ማሰባሰብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
 
በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ኢትዮጵያ ማሳያ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ቢያጋጥማትም ከእድገቷ ግን እንዳላስቆሟት ጠቁመዋል፡፡
 
በመሆኑም በውጭው ዓለም በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ያለውን ትርክት በአዲስ መልክ ለመቅረጽ ቆርጠን ተነስተናል ነው ያሉት፡፡
 
ትርክቶች እጣ ፈንታችንን እንደሚቀርፁ ከዚህ በፊት አጋርቻለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ከረጅም ጊዜ በፊት፣ እኛ እንደ አፍሪካውያን በእኛ ያልተሰራ ስለራሳችን የሚነገሩ ትርክቶችን ተቀብለናል ሲሉ ገልጸዋል።
 
ይህ አካሄድም በሁለት ወሳኝ መንገዶች መለወጥ አለበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው።
 
የመጀመሪያው በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እና በቡድን 7 እንዲሁን ቡድን 20 አባል ሀገራት ተመጣጣኝ ውክልና በማግኘት ሲሆን ÷ሁለተኛው ደግሞ የአፍሪካ ህብረትአህጉራዊ ሚዲያ ተቋምን ዕውን በማድረግ ነው ብለዋል።
 
ከጊዜ ወደ ጊዜ በውስብስብና በፈጣን ሁኔታ በሚለዋወጥ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ውስጥ አንድነት ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
 
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት ስናከብር ሁሉም የአፍሪካ መሪዎችና ሕዝቦች ቀደምት አባቶቻችን ያቀረቡትን የአንድነት መልዕክት ተግባራዊ በማድረግ ሊሆን ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.