Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ደመቀ መኮንን ከቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ (ሲድካ) ሊቀመንበር ሊዎ ጃወሁይ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ወቅት አቶ ደመቀ ፥ ቻይና በሀገራት የውስጥ ነጻነት ጣልቃ ሳትገባ የጋራ ተጠቃሚነት መርሆዎች ላይ በመመስረት ለኢትዮጵያ በምትሰጠው ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ቻይና በደቡብ-ደቡብ የትብብር ማዕቀፍ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

በቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (ፎካክ) ይፋ የተደረጉት ዘጠኙ ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውን እስከ ፕሮጀክቶቹ ፍጻሜ ድረስ ተቋሙ ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተሳካ ሁኔታ እየተተገበረ መሆኑን ያነሱት አቶ ደመቀ ፥ ቻይና ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የመልሶ መቋቋምና ዳግም ግንባታ ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሊቀመንበር ሊዎ ጃወሁይ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ የቻይና ጠንካራ አጋር ብቻ ሳትሆን በአፍሪካ ትልቅ ተፅዕኖ ያላት ሀገር በመሆኗ ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

የቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ በትምህርት፣ በግብርና፣ በተፋሰስ ልማት እና ሌሎችም መስኮች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.