Fana: At a Speed of Life!

ከቀዳማዊ ኃይለ-ሥላሴ እስከ ቶማስ ሳንካራ – የአፍሪካ ድንቅ ልጆች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ በተለያዩ ጊዜያት ሀገራቸውንም ሆነ አህጉራቸውን ያገለገሉ የተለያዩ ድንቅ መሪዎችን አፍርታለች፡፡

አፍሪካ በድህነት፣ በጦርነት፣ በመልካም አስተዳደር ጉድለት እና በሙስና ስሟን ከሰፈረበት መዝገብ ለመፋቅ በተለያዩ ጊዜያት በእልህ የተነሱላት ልጆች ነበሯት ፤ አሏትም፡፡

ለዛሬው የቀደሙትን እናውሳ፡፡

ኔልሰን ማንዴላ

ኔልሰን ማንዴላ ከአፍሪካ የደቡብ ማህጸን የወጡ መሪ ናቸው፡፡ ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፥ ከዚያ በፊት አፓርታይድን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ለ27 ዓመት የወጣትነት ጊዜያቸውን በእስር አሳልፈዋል፡፡

ከረጅም ዓመታት እስር በኋላ የፓርቲያቸው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (ኤ ኤን ሲ) ፓርቲ በፈረንጆቹ 1994 የተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎም ሀገራቸውን መምራት የሚችሉበትን እድል አግኝተዋል።

ምርጫውም በደቡብ አፍሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ እንደሆነ ይነገርለታል።

ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ “ማዲባ” የሚል የቁልምጫ ስም ያላቸው ተወዳጅ መሪም ነበሩ።

ስለእርሳቸው ሲነሳም ደቡብ አፍሪካውያን ደስታ እና የእኔነት ስሜት ማዲባ እኮ… ብለው የተከፈለላቸውን ወጣትነት፣ እንግልት እና ስቃይ በሚችሉት ቃላት ይገልጻሉ፡፡ ማዲባ የሁሉም ቤት የቤተሰብ አባል ናቸው ፤ ማዲባ የፍቅርና የይቅርታ ምሳሌያቸው ሲሆኑ የሀገሬው ዜጎች ስለእርሳቸው ተናግረውና ገልጸው የማይረኩበት ድብቅ ስስትና ፍቅር አላቸው።

ፈገግታና የዋህ መልካቸው ከልብ ለመሆኑ የሀገሩ ሰው አይደለም የዓለሙ ማህበረሰብ የሚመሰክረው ነው፡፡

ኔልሰን ማንዴላ በአፓርታይድ ዘመን የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚያጣራ የእርቅ ኮሚሽን በማቋቋም ለ27 ዓመታት በብረት አጥር ውስጥ በስቃይ አኑረው የወጣትነት ዕድሜያቸውን ለሰረቁት ሁሉ ይቅር ብያችኋለሁ በማለት እድሜያቸውን ቀምተው ግፍ ለፈጸሙባቸው በቀል ሳይሆን ምህረት አድርገው ለዓለም ይቅርታን እና የይቅርታን አስፈላጊነት አሳይተዋል።

ማንዴላ ለዓስርት ዓመታት የዘለቀውን የአፓርታይድ ጭካኔን በመታገልና በደቡብ አፍሪካ ሰላም በማምጣት በ1993 የኖቤል የሰላም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ቀዳማዊ ኃይለ-ሥላሴ

ኢትዮጵያዊው ባለግርማሞገሱ ንጉስ ይሏቸዋል፤ ስለእሳቸው ያነሱ ሁሉ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ-ሥላሴ ለትምህርት እና ለዘመናዊነት ያላቸው ትኩረት የተለዬ ለመሆኑ በብዙ የታሪክ ድርሳናት ተጽፎ ይገኛል፡፡ ቀኃሥ ፓን አፍሪካዊ እንደነበሩ ሲነሳ አፍሪካን ከአፍሪካውያን እና ከተቀረው የዓለም ማህበረሰብ ጋር በሰፊው በማስተሳሰር ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ብቃታቸውን ለዓለም ማስመስከር ችለዋል።

በዚህም ንጉሱ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር አባል እንድትሆን እና በፈረንጆቹ 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ምስረታ በፕሬዚዳንትነት በመምራት የድርጅቱ የመጀመሪያ ሊቀመንበርም ነበሩ፡፡

ለአፍሪካውያን አንድነት መሰረት ከጣሉትም ቀዳማዊ ኃይለ-ሥላሴ ግንባር ቀደሙ ናቸው።
ኩዋሜ ንክሩማህ

ክዋሜ ንክሩማህ የጋና የመጀመሪያው የሀገሪቱ ተወላጅ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ ሀገራቸውን ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ እንድትወጣ በማድረጋቸው ከፍተኛ ተቀባይነት ነበራቸው። የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ሲመሰረትም ከመስራቾቹ አንዱ ነበሩ፡፡

ንክሩማህ ለ12 ዓመታት በውጭ ሀገር ተምረው ወደ የወርቅ ምንጯ ሀገራቸው በመመለስ ጋና ከነበረባት አስከፊ የቅኝ ግዛት እስራት ለማውጣት የታገሉ መሪ ናቸው ፡፡

በዚህም ግዙፍ ፕሮጀክቶችንና የልማት ስራዎችን በፕሬዚዳንትነት ቆይታቸው ሰርተዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በ1962 ከሶቭየት ህብረት የሌኒን የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።

ጁሊየስ ኔሬሬ

ጁሊየስ ኔሬሬ የታንዛኒያ (የቀድሞዋ ታንጋኒካ) ከ1961 እስከ 1985 የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። ፓንአፍሪካዊው ኔሬሬ በ1953 ታንጋኒካ የአፍሪካ ብሄራዊ ህብረት በመመስረት ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶም ታንጋኒካ 1961 ነፃነቷን አግኝታለች።

በተጨማሪም ኔሬሬ በ1964 ዛንዚባር እና ታንጋኒካን አንድ በማድረግ ዛሬ ታንዛኒያ ብለን የምትጠራው አፍሪካዊ ሀገር ለመመስረቷ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡

ፓትሪስ ሉሙምባ

ፓትሪስ ሉሙምባ አብዮታዊ የኮንጎ ፖለቲከኛ ሲሆኑ ፥ የሀገሪቱ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትርም ናቸው፡፡ ሉሙምባ እንግሊዛዊ ዜግነት በነበራቸው ወቅትም የኮንጎ ንግድ ህብረት ፕሬዚዳንት በመሆን ማገልገላቸው ይነገራል።

ወደ ኮንጎ ከተመለሱ በኋላም የኮንጎ ብሄራዊ ንቅናቄን (ኤም ኤን ሲ) በመመስረት የፓን አፍሪካን ርዕዮተ ዓለምን በመጠቀም ለሀገራቸው ነፃነት መታገልን መርጠው ወደዛው ገብተው ታግለዋል።

አሁን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመባል የምትታወቀው ኮንጎ በ1961 ነጻ ሀገር ሆና እንድትቀጥል ምክንያትም ነበሩ፡፡ ሉሙምባ በድንቅ ስብዕና እና በመግባባት ችሎታቸው ከሚነሱ ምስጉን መሪወች መካከል በግንባር ቀደምነት ይነሳሉ፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ገና በ35 ዓመታቸው በምዕራባውያን እና በውስጥ ኃይሎች በተቀነባበረ ሴራ መገደላቸው እስካሁን የሀገሬው ሰው የእግር እሳት ነው ይባላል፡፡

ጆሞ ኬኒያታ

የፀረ-ቅኝ ግዛት ታጋይ እና አቸታጋይ የነበሩት ጆሞ ኬኒያታ የመጀመሪያው የኬንያ ፕሬዚዳንት እና ከ1963 እስከ 1964 ደግሞ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። በዚያን ወቅት እንግሊዝ ባህር አቋርጣ ድንበር ጥሳ ልግዛችሁ ስትል አሻፈረኝ በሚለው ትግላቸው ይታወሳሉ፡፡

ዘረኝነትንና መድሎን አምርረው የሚጠሉት ኬኒያታ ሀገራቸው ከቅኝ ግዛት ለመውጣቷ ትልቅ ሚና የተወጡ ፓን አፍሪካኒስት ነበሩ።

በተጨማሪም በሀገራቸው ህዝቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍን እና ኬኒያ የአፍሪካ ህብረት አባል እንድትሆን አድርገዋል፡፡

ቶማስ ሳንካራ

በርካቶች መሞቅ ሳይጀምር የከሰመው የአፍሪካው ኮከብ፤ አፍሪካዊው ቼ ጉቬራ ይሏቸዋል የቡርኪናፋሶውን ፕሬዚዳንትና ልበሙሉውን ወጣት መሪ ቶማስ ሳንካራ።

ሳንካራ ከ1983 እስከ 1987 የቀድሞዋ የላይኛው ቮልታ የአሁኗ ቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡

ከዚያ በፊት በ20 ዓመታቸው ወደ ጦር ሰራዊቱ በመቀላቀል በ1970 በማዳጋስካር የውትድርናን ልክ ማየታቸው ይነገራል፡፡

ፈገግታ የማይለያቸው ሳንካራ ስልጣን ሲይዙ በቀኝ ገዢዎች የወጣውን የሀገራቸውን ስም ከአፐር ቮልታ ወደ ቡርኪናፋሶ ቀይረዋል፡፡ የተከበሩ እና የታማኝ ህዝቦች ምድር እንደማለት!

ሳንካራ ለቡርኪናውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንም ተራማጅ እና አሻጋሪ ሃሳቦችን ይዘው ቢመጡም አሻጋሪ መሪዎችን የማያስቀምጠው ሴራ ህይወታቸውን ነጥቋቸዋል።

ሳንካራ በአንድ ወቅት ከአንድ ወዳጃቸው ጋር ሲያወጉ የቼን መገደል ሰምተው ኖሮ በማዘን “እኔስ እዛ እድሜ የምደርስ አልመሰለኝም” ማለታቸው ይነገራል፡፡

እንደገመቱትም በ37 ዓመታቸው በምዕራባውያን ተቀነባብሯል በተባለ የመፈንቅለ መንግስት ሴራ በአጋራቸው ብሌዝ ኮምፓኦሬ ከ12 ከፍተኛ ሹማምንቶቻቸው ጋር ተገድለዋል።

በዛሬው ዕለት እየተከበረ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ድህነትን፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን እና ሙስናን በመታገል ሊሆን እንደሚገባ በተለያዩ የአህጉሪቱ መሪዎች ተነስቷል፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.