Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት የሕግ መወሰኛ ም/ቤት አባል ወ/ሮ ማርታ ገብረጻዲቅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት የመጀመሪያዋ ሴት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የነበሩት ወይዘሮ ማርታ ገብረጻዲቅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
 
ወ/ሮ ማርታ ገብረጻዲቅ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ91 ዓመታቸው ነው ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡
 
የወ/ሮ ማርታ ገብረጻዲቅ የአስክሬን ሽኝት መርሐ ግብርምበዛሬው ዕለት ጦርሃይሎች አካባቢ በሚገኘው ቀጣና ሁለት አጥቢያ ሙሉወንጌል ቤተክርስቲያን ተካሂዷል፡፡
 
በመርሐ ግብሩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል፡፡
 
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።
 
ወ/ሮ ማርታ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል በአሜሪካ አጠናቀው ወደ ሀገር እንደተመለሱ በትምህርት ሚኒስቴር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በከፍተኛ ኃላፊነት አገልግለዋል።
 
ኢትዮጵያንም በመወከል ከፍተኛ ልዑካንን ይዘው የሀገራቸውን ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ በተለይ በእስራኤል፣ ካናዳ፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያንና በሌሎች የአውሮፓና የእስያ ሀገራት በመንቀሳቀስ ሙያዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
 
ወ/ሮ ማርታ በተለይ ከህጻናት፣ ከሴቶች፣ ከአካል ጉዳተኞች እና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለሰሯቸው የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ከታይለር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡
 
የወ/ሮ ማርታ ቀብር ስነ ስርዓትም በዛሬው ዕለት ከቀኑ 8:00 ዊንጌት በሚገኘው በጴጥሮስ ጳውሎስ መካነ መቃብር መፈጸሙን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ወ/ሮ ማርታ ገብረጻዲቅ÷ ባለትዳርና አምስት ከአብራካቸው የተገኙ እና 7 የማደጎ ልጆች እንዲሁም 9 የልጅ ልጅ ልጅ የታደሉ የዕድሜ ባለጸጋ ነበሩ፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.