Fana: At a Speed of Life!

የክልሉ መንግሥት ማልማት ለሚችሉ ቁርጠኛ ባለሐብቶች አስፈላጊውን መሬት ያቀርባል-ይልቃል ከፋለ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉ መንግሥት ማልማት ለሚችሉ እውነተኛ እና ቁርጠኛ ለሆኑ ባለሐብቶች አስፈላጊውን መሬት ያቀርባል ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ(ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ በዛሬው እለት አርዲ እምነበረድና ቀለም ፋብሪካን ጎብኝተዋል።

ይህን ተከትሎ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ(ዶ/ር)በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ፋብሪካው በግንባታው ዘርፍ ያለውን የግብአት ጉድለት በመሙላት እረገድ ጉልህ ድርሻ ማበርከት የሚችል ነው ብለዋል።

በሀገራችን የልማት መስፋፋት ትልቁ ማነቆ ካፒታል ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በዚህም ምክንያት አቅም ያለው ባለሐብትና የቴክኖሎጂ አቅማችን በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል።

አርዲ እምነበረድና ቀለም ፋብሪካ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሙሉ አቅም ለማምረት መብቃቱ ትልቅ እድገት ነውም ብለዋል።

ይህም በበርካታ ጉዳይ ጥገኛ የነበረውን ኢኮኖሚያችንን በአገር ውስጥ ምርት መሸፈን እንደምንችል ማሳያ ጭምር ነው ብለዋል።

አማራ ክልል በማዕድን ሐብት ታዋቂ አልነበረም፤ ነገር ግን ከክልላችን አልፎ አገሪቱን ሊለውጥ የሚችል የማዕድን ሐብት አለን፤ ይሔንን በመረዳት ባለሐብቶች በተለያዩ ዘርፍ ተሰማርቶ ማልማት እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

ዘርፉን ለማልማት የሚመጡ አቅም ያላቸው ባለሐብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት አግኝተው ወደስራ እንዲገቡ እንደሚደረግም ገልፀዋል፡፡

በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ቦታ ወስደው በተፈለገው ጊዜ ወደስራ ያልገቡ ባለሐብቶች ግንባታቸውን አጠናቀው ወደምርት እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መሬት የምንሰጠው ፋብሪካ ተጠናቆ ምርት እንዲመረትበት፣ የስራ እድል እንዲፈጠርበት ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግሥት ማልማት ለሚችሉ እውነተኛ እና ቁርጠኛ ለሆኑ ባለሐብቶች አስፈላጊውን መሬት እንደሚያቀርብም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.