Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን ወክለው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ የአይ ሲ ቲ ፍጻሜ ውድድር የተሳተፉ ተማሪዎች 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ወክለው በ7ኛው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ የአይ ሲ ቲ ፍጻሜ ውድድር የተሳተፉት ተማሪዎች የሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ።

ከግንቦት 16 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በቻይና ሼንዘን ከተማ የሁዋዌ አይ ሲ ቲ ዓለም አቀፍ ውድድር የተካሄደ ሲሆን÷ ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩት ተማሪዎች የሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

በውድድሩ ከ36 አገሮች የተውጣጡ 146 ቡድኖችም ተሳትፈዋል፡፡

በኢኖቬሽን ትራክ የተወዳደሩት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የራሳቸውን የፈጠራ ሃሳብ ይዘው የቀረቡ ሲሆን÷ “የግእዝ ፊደላት ክላሲፋየር” የተሰኘ መወዳደሪያ ይዘው ቀርበዋል፡፡

የሁዋዌ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሊዩ ጂፋን÷ድርጅቱ የአይሲቲ ዘርፉን ለማጠናከርና ተተኪዎችን ለማፍራት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ ከጎንደር፣ ዋቸሞ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ጥራት ያለው የአይሲቲ ታለንት እድገትን ለማፋጠን፣ ለኢንዱስትሪው ብቁ ተሰጥኦዎችን ለማዘጋጅትና መምረጥ፣ የመስኩ ባለተሰጥኦዎችን ወደፊት ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ንቁ ተሳታፊዎችን ለማበርከት፣ የመስኩ ፍላጎትና አቅርቦት በቂ እንዲሆን ለማበረታታትና በዘላቂነት አስተዋፅኦ ለማድረግ ይሰራልም ነው የተባለው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.