Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉባዔን ልታስተናግድ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉባዔን ልታስተናግድ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በየዓመቱ የሚያካሂደውን ብሔራዊ የሥራ ጉባዔ በዚህ ዓመት በአፍሪካ ደረጃ ለማካሔድ ዝግጀት ማድረጉ ተመላክቷል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሡ ጥላሁን እንዳሉት ፥ አፍሪካ አብዛኛው የሕዝብ ቁጥሯ ወጣት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ሀገራት ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ጉባዔው በአፍሪካ ደረጃ መዘጋጀቱ በአህጉሪቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር ሂደት አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ በጋራ ለመስራት ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

የአፍሪካ ህብረት አፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጠናን መርሕ አጀንዳ ባደረገበት ወቅት ጉባዔው በጋራ መዘጋጀቱ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ያነሱት አቶ ንጉሱ÷ ጉባኤው በአባል ሀገራት መካከል ጥምረት ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተለይም በአህጉሪቱ በግብርና ፣ ኢንዱስትሪ ፣ ኮንስትራክሽን እና ሌሎች ዘርፎች የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች እንዲጨምሩ ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካይ አንቶኒዮ ፔድሮ በበኩላቸው÷ ምቹና ዘላቂ የሥራ ዕድል ለአፍሪካውያን ለመፍጠር ፖሊሲዎችን ማሻሻል እና ወጣቶችን የሚያሳትፉ አዳዲስ የሥራ መስኮችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

በፈትያ አብደላ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.