Fana: At a Speed of Life!

የተጋነነ የዋጋ ተመን በመጠየቅ ሕብረተሰቡን አማረዋል የተባሉ ጫኝና አውራጅ ማህበራት ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተጋነነ የዋጋ ተመን በመጠየቅ ሕብረተሰቡን ለምሬት ዳርገዋል የተባሉ ጫኝና አውራጅ ማህበራት ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ ሕብረተሰቡ ከግምት በላይ እንዲከፍል ማስገደድ ፣ የሥነምግባር መጓደልና መሰል ችግሮች በማህበራቱ ላይ መስተዋሉን ከሚቀርቡ ቅሬታዎች መረዳት ተችሏል።

በከተማው በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ከ6 ሺህ 423 በላይ አባላት ያላቸው 1 ሺህ 72 ማህበራት ቢኖሩም ሕጋዊነታቸውን እንደሽፋን በመጠቀም የተወሰኑ ማህበራት ሕብረተሰቡ ላይ ጫና በሚያደርስ ተግባር መሰማራታቸውን ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።

ማህበራቱ ያልተገባ የዋጋ ተመን ከመጠየቃቸው ባለፈ በስራቸው ማንነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦችን መቅጠር፣ በጋራ መኖሪያ ቤት ቤት የሚቀይሩ ግለሰቦችን ለመጫንም ሆነ ለማውረድ ከ90 እስከ 100 ሺህ ብር መጠየቅ እና ለሕግ ተገዢ አለመሆን በማህበራቱ የተስተዋሉ ዋነኛ ችግሮች ናቸው ብለዋል።

በዚህም የሕብረተሰቡን ምሬት ከግንዛቤ በማስገባት የአስተዳደሩ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ችግሩን ለመቅረፍ ተደጋጋሚ ውይይት ቢያደርግም ከድርጊታቸው ባልተቆጠቡና ለሕግ ተገዢ ባልሆኑ 505 አባላት ባላቸው 44 ማህበራት እና 97 ግለሰቦች በሕግ ጥላ ስር እንዲውሉ መደረጉን ኃላፊዋ ተናግረዋል።

በቀጣይም በመሰል ድርጊቶች ላይ በተሰማሩት ማህበራት ላይ እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል ተብሏል።

በወንድሙ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.