Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ የሽግግር ፍትኅ የሕዝብ ምክክርና ግብዓት የማሰባሰብ ሥራ በተለያዩ ክልሎች ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የሚካሄደው ሀገራዊ የሽግግር ፍትኅ የሕዝብ ምክክርና ግብዓት የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን የፍትኅ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የሽግግር ፍትኅ ሥርዓትን መተግበር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም፣ ዴሞክራሲ እና ዕድገት ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን በመገንዘብ ሒደቱን በተሟላና በተቀናጀ መልኩ ለመተግበር የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

በዚህ ረገድ የሽግግር ፍትኅ ፖሊሲ የማርቀቅ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ‘የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች’ መነሻ ሠነድ የፍትኅ ሚኒስቴር ባደራጀው ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተዘጋጅቷል፡፡

ለሀገራዊ የሽግግር ፍትኅ ፖሊሲ ዝግጅት የሚያስፈልገው ብሔራዊ ምክክር የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓትም ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

ይህን ተከትሎም በክልሎች ደረጃ የሚካሄደው ምክክር በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ከ58 በላይ ከተሞች ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለማከናወን መርሐ-ግብር መውጣቱ ተገልጿል፡፡

በመርሐ-ግብሩ መሠረት የሕዝብ ምክክሩ የመጀመሪያው ምዕራፍ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች በስኬት መከናወኑም ነው የተገለጸው፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በሲዳማ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እና በደቡብ ብ/ብ/ህ ክልል በተመረጡ 12 ከተሞች እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡

በምክክሮቹም ላይ ፍጹም ነፃ እና ገለልተኛ በሆነ ሂደት የሚለዩ እና የሚጋበዙ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚወክሉ ግለሰቦች እና ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ተሳታፊዎችም በባለሙያዎች በሚቀርቡ አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቦች ላይ ክርክር በማካሄድ በነፃነት የፖሊሲ አማራጭ ሠነዱን ለማዳበር የሚያስችሉ ግብዓቶችን እንዲያጋሩ ይጠበቃል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.