Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ እና ኩዌት መካከል የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት በአጭር ጊዜ እንዲፈረም ጠየቁ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ኩዌት መካከል የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት በአጭር ጊዜ እንዲፈረም የውጭ ጉዳይ ሚኒትስር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጠየቁ።

ሚኒትስር ዴኤታው በኢትዮጵያ ከኩዌት አምባሳደር ናይፍ ሃኘስ አል ኦይታይቢ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ እና ኩዌት መካከል የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈረም የሚደረገው ዝግጅት እንዲፋጠን ጠይቀዋል።

የሁለቱ ሀገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በሚጀመርበት ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ ከወዲሁም አስፈላጊ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እና ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት የኩዌት መንግስት እንዲደግፍም አምባሳደር ምስጋኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ናይፍ ሃኘስ አል ኦይታይቢ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት በአጭር ጊዜ እንዲፈረም የኩዌት መንግስት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና ኩዌት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ እንዲጀመር አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.