Fana: At a Speed of Life!

በፀጥታ ችግር ለ3 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የጋምቤላ-ሸበል-ደንቢዶሎ መንገድ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በፀጥታ ችግር ምክንያት ለሦስት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው ከጋምቤላ ክልል ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚወስደው መንገድ ለማኅበረሰቡ ክፍት መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በቀጠናው በተሰጠው ግዳጅ መሠረት ግዳጁን ተወጥቶ ከጋምቤላ ክልል ወደ ኦሮሚያ ክልል ሸበል ደንቢዶሎ የሚወስደውን መንገድ ከሥጋት ነፃ ማድረግ እና ሠላም ማስፈን መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

በመከላከያ ሠራዊት የዳሎል ማዕከላዊ እዝ 104ኛራስ ደጀን ኮር 35ኛ ዋሊያ ክፍለ-ጦር ዋና አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ደሳለኝ ሙላው ÷ በአካባቢው አስተማማኝ የሠላም ማስከበር ሥራ መሠራቱን መግለፃቸውን የጋምቤል ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

ሠራዊቱን በመደገፍ ለሠላም አስተዋፅዖ ያበረከቱ የመንግስት ኃላፊዎችንና ሕዝቡንም አመሥግነዋል፡፡

የመንግስት ኃላፊዎችና ማኅበረሰቡ በሠላም መደፍረስ ምክንያት ዳግም መንገዱ እንዳይዘጋ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እና መረጃ መለዋወጥ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ዮናስ አበበ ÷ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ለአከባቢው ሠላም መስፈንና ለመንገዱ መከፈት ላደረጉት ተጋድሎ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ከአጎራባች ክልሎች ህዝቦች ጋር ያለውን ትሥሥር ለማጠናከር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በኦሮሚያ ክልል የአንፊሎ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ነጋሽ ቀንዓ በበኩላቸው ÷ የኦሮሚያን ክልል ከጋምቤላ ክልል ጋር የሚያገናኘው መንገድ መቋረጡ በሕዝቡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ቀውስ ማስከተሉን አብራርተዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በአካባቢዎቹ በሠራው ሠላም የማስከበር እና ፀጥታ የማረጋገጥ ሥራ ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.