Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የ8ኛ ክፍል ፈተና ከፊታችን ሰኔ 26 እስከ 27 ቀን ይሰጣል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2015 የትምህርት ዘመን ክልላዊ የ8ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 26 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ/ር)÷ ክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 26 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ፈተናው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በክልል ደረጃ እንደሚዘጋጅ ጠቅሰው÷የፈተና ጥያቄዎችም በአዲሱ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ ምክንያት 8ኛ ክፍል ከተማሩት ብቻ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡
ወላጆች፣ መምህራንና አመራሮች በቀሪ ጊዜያት ለ8ኛና 12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በተዘጋጁበት ልክ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ተፈታኝ ተማሪዎች የማለፊያ ነጥቡ 50 በመቶ እና በላይ መሆኑን አውቀው÷ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ቀሪ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡
ከሰኔ 26 እስከ 27 ቀን በሚሰጠው የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና 347 ሺህ 966 ተማሪዎች በ5 ሺህ 752 ትምህርት ቤቶች እንደሚወስዱም የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.