Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ሊዋጋው እንደሚገባ አስገነዘቡ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አይ ኤስ አይ ኤስ፣ አልሸባብ እና ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች፥ ተዋጊዎችን ለመቅጠር እና ገንዘብ ለማግኘት የሚጠቀሙበትን መንገድ መዝጋትና ይህን አካሄድ መዋጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሚኒስትሩ በሳዑዲ እየተካሄደ ባለው አይ ኤስ አይ ኤስ የሽብር ቡድንን ለመዋጋት በተቋቋመው ዓለም አቀፍ ጥምረት የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው።

አቶ ደመቀ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለማስወገድ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

መሰል ቡድኖች አፍሪካን ጨምሮ በሌሎች ቦታዎች ሰርገው እንዳይገቡ፣ እንዳይስፋፉ እና የግንኙነት መረብ እንዳይዘረጉ የሚከላከሉ ቡድኖችን መቀላቀሉ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

አያይዘውም እነዚህ ቡድኖች በእኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራት ያደረሱትን ስቃይ ልንጋራው ይገባልም ነው ያሉት።

85 አባል ሀገራት ያሉት ይህ ዓለም አቀፍ ጥምረት የአሸባሪ ቡድኑን የግንኙነት መስመር ማጥፋት፣ የሚነዛቸውን ፕሮፓጋንዳዎች ማክሸፍና ድንበር ተሻግረው ጥቃት የሚያደርሱ የቡድኑን አባላት እንቅስቃሴ መግታትን አላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

አቶ ደመቀ መኮንን ዛሬ ከሚካሄደው ጉባዔ ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ሳዑዲ መግባቱ ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.