Fana: At a Speed of Life!

በመንግስት ተቋማት የሥራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ጭምር የሚዘወረው ሕገ ወጥ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሕገ ወጦች እጃቸውን ያስረዘሙበትንና አሻጥር ፈጥረው የሚዘውሩትን የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት በመፈተሽ የምርመራ ዘገባዎችን በማቅረብ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

በዘገባዎቹ ዘርፉ በደላሎች፣ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ የመንግስት ስራ ሃላፊዎችና ተቋማት ተሳታፊነት እንደሚከወን በማስረጃዎች ያረጋገጠ ሲሆን÷ ከእነዚህ ተቋማት አንዱ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሰራተኞች ናቸው::

ተቋሙ ሕገወጦችን መቆጣጠር ለምን አልቻለም? ለመፍትሄውስ ምን እየሰራ ነው? በሚል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አሰግድ ጌታቸውን ጠይቋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው በምላሻቸው÷ ሕገ ወጥነትን ለመቀነስ ሥርዓቱን ወደ ዲጂታል መቀየር እና መሰል ስራዎች እየተሰሩ ነው ፤ የሀሰተኛ መረጃዎችን ለመቀነስም ከ3 ወራት በፊት አዲስ ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ÷ የሕግ ክፍተቶችን የማስተካከል እንዲሁም ጥፋት የተገኘባቸው ሰራተኞች እንዲታገዱ የማድረግ ስራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡

ለዚህም ÷በ2014 ዓ.ም በጀት አመት 17 ሠራተኞች ላይ የእገዳ ውሳኔ መተላለፉን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስታወሱት፡፡

ከዚህ ቀደም በሚኒስቴሩ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት የስራ ውል ምዝገባና ማጽደቅ ከፍተኛ ባለሙያ የነበሩት አቶ ገሰሰ ደሬሳ በህገወጥ መንገድ ሰዎች እንዲዘዋወሩ ሰራተኞች ያመቻቹ እንደነበር ቢናገሩም እሳቸው ከኤጄንሲዎች ጋር የጥቅም ግንኙነት እንደነበራቸው ኤፍ ቢ ሲ ጥቆማ ደርሶታል።

አቶ ገሰሰ ደሬሳ የከፍተኛ ባለሙያ ከነበሩበት ቦታ ተነስተው ወደ ሌላ ሲዘዋወሩ የሽኝት መርሐ ግብር በሚል ሰበብ ገንዘብና ለእሳቸው እና ለባለቤታቸው የወርቅ ስጦታ ከኤጀንሲዎች እንደተበረከተላቸውም ኤፍ ቢ ሲ መረጃ ደርሶታል፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም ኤፍ ቢ ሲ ባደረገው የማጣራት ስራ ለአቶ ገሰሰ ደሬሳ እና ለባለቤታቸው ስለተበረከተላቸው የወርቅ ስጦታ ማረጋገጥ ችሏል፡፡

እሳቸውም ስለተበረከተላቸው የወርቅ ስጦታ ሽልማት ነው በማለት ያመኑ ሲሆን÷ የተደረገልኝም ትጉህ ሰራተኛ በመሆኔ ነው፤ ገንዘብ ግን አልተቀበልኩም ብለዋል፡፡

የእርስዎ ሽልማት ነው እንበል ለባለቤትዎስ ከኤጀንሲዎች የተሰጣቸው የወርቅ ስጦታ ምንን ይገልጻል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “ባለቤቴ ሁሉ ነገሬ ስለሆነች፣ ጠዋት የምትቀሰቅሰኝም በመሆኗ ቢያንስባት እንጂ አይበዛባትም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ገሰሰ ደሬሳ ከዚህ ቀደም ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ የሚሰማሩ ዜጎችን ማስረጃዎች ሲያፀድቁ የነበሩ ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው፤” የሚሰራ ሊሳሳት ይችላል፤ ሆን ብዬ ግን አልተሳሳትኩም “ሲሉም ተከራክረዋል።

ለመሆኑ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የሰራተኛውን ጉዳይ ያውቀው ይሆን? በሚል ሚኒስትር ዴኤታው አሰግድ ጌታቸው ለቀረበላቸው ጥያቄም ÷ በርካታ ጥቆማዎች በግለሰቡ ላይ ደርሰውናል ፤ ማስረጃ ግን አላገኘንም ብለውናል፡፡

ለጊዜው ግን ግለሰቡን ከደንበኛ ጋር ፊት ለፊት የማይገናኙበት ቦታ እንደመደቧቸው እና ሚኒስቴር መሰል እርምጃዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ሌላው በሕገወጦች መረብ ተሳታፊ ተዋንያን እንዳሉበት የሚነሳው የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ነው።

በተለይም ወደ ሀገር ለመውጣት የመጨረሻውን ውሳኔ የሚወስኑ ሰራተኞች ከዚህ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ይነሳል።

በአገልግሎቱ የኬላዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ቦጋለን በዚህ ድርጊት ተሳታፊዎችን ታውቋቸዋላችሁ? ስንል ጠይቀናል።

እርሳቸውም እርምጃ የተወሰደባቸውና እርምጃ ለመውሰድ በሂደት ላይ ጉዳያቸው ያለ እንዳሉ ነግረውናል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በምርመራው÷ ችግሩ ጥልቅና ሰፊ፤ ባለድርሻዎች እና ተዋንያኖችም በርካቶች መሆናቸውን ተገንዝቧል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በቀጣይ የግል ተቋማት እና ኤጄንሲዎችን በመፈተሽ መሰል ዘገባ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.