Fana: At a Speed of Life!

በሕገ-ወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት የተጠረጠሩ 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ሁለት ኢትዮጵያውያን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የሰላም መደፍረስ እና የጸጥታ ሥጋቶችን ለመቀልበስ ትኩረት እያደረገ በነበረበት ወቅት በሕገወጥ የማዕድን ምርትና ዝውውር የተሰማሩ አካላት በሀገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎችና አሸባሪ ቡድኖች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር በኢኮኖሚው መስክ አስተዋፅዖ ባላቸው የማዕድን ምርቶች በተለይም በወርቅ ላይ ያተኮረ ዝርፊያ ሲፈጽሙ መቆየታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የማዕድን ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የነበረው ድርሻ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ እንዲሁም በዘርፉ የሚታዩ ሕገወጥ ድርጊቶች ወደ ብሔራዊ የደኅንነት ሥጋት እንዳይሸጋገሩ ችግሮችን የሚለይና መፍትሄ የሚያስቀምጥ ሀገር ዓቀፍ ካውንስል ተቋቁሞ ተግባራዊ አንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ካውንስሉ በሰጠው አቅጣጫ መሰረትም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የድርሻውን ስምሪት በመውሰድ በተለይም ከወርቅ ምርት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ሕገ ወጥ ድርጊቶችንና የጥቅም ትስስሮችን በተመለከተ ጥልቀት ያለው ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱም ነው የተነሳው፡፡

ጥናቱን መነሻ በማድረግም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በጥናቱ ለየሁት እንዳለው÷ ቁልፍ የማዕድን ሀብቶች ኢኮኖሚውን እንደ ሀገር ለመደገፍ እምቅ አቅም ያላቸው ቢሆንም የምርት ሂደቱና ግብይቱ ሕጋዊ ስርዓትን ተከትሎ እየተካሄደ እንዳልነበረ ለማረጋገጥ ተችሏል ብሏል፡፡

በተለይም ወርቅን ሕገወጥ በመሆነ መንገድ ከማምረት ባሻገር የሀገሪቱን ሕጋዊ ሥርዓት በመከተል ወደ ብሔራዊ ባንክ ከማስገባት ይልቅ ከሽብር ቡድኖችና ለሕገወጥ ድርጊቱ ተባባሪ ከሆኑ አካላት ጋር በመቀናጀት በሀገር ሀብት ላይ ዘረፋ ሲፈጸምና ሀገራዊ የደኅንነት ሥጋቱ እንዲባባስ አስተዋጽዖ ሲያደርግ እንደነበርም ተደርሶበታል ነው ያለው፡፡

እምቅ የማዕድን ሀብት ከሚገኝባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የሆነ የምርትና የግብይት ችግር የሚታይበት መሆኑ በጥናቱ መለየቱም ተጠቁሟል፡፡

በክልሉ እውቀት፣ገንዘብና ቴክኖሎጂ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በወርቅ ምርት ከመሰማራታቸው በተጨማሪ÷ የአካባቢው ነዋሪዎች በማህበር በመደራጀት በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማምረት ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ እንደሚገኙ አገልግሎቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.