Fana: At a Speed of Life!

የዲስክ መንሸራተት እና ህክምናው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዲስክ ፕላስቲክ የመሰለ ተለጣጭ ወይም ለስለስ ያለ በጀርባችን ባሉ አጥንቶች መካከል የሚገኝ እና አጥንቶቹ እርስ በእርሳቸው እንዳይፋተጉ እና ለነርቭ ጉዞ እንዲመች የሚያደርግ የጀርባ አጥንት ክፍል ነው፡፡

ዲስክ በተለያየ ሁኔታ ሊጎዳ የሚችል ሲሆን ዲስኩ በጉዳት ምክንያት ያለበትን ቦታ በመሳት ወደ ጎን አልያም ወደ ጀርባ አጥንት በመጠጋት የነርቭ ህዋሳትን ይጫናል፡፡

ይህ ነርቭ ላይ በመጫን የሚከሰተው አልያም የሚፈጥረው ህመም ወይም አጠቃላይ ሁኔታዎች የዲስክ መንሸራተት ወይም /herniated disc/ ይባላል።

ነርቭ የተለያዩ የሰውነታችንን ክፍል ያሚያንቀሳቅስ ሲሆን በዲስክ መንሸራተት ወቅት በብዛት ወደ እግራችን የሚሄደው ነርቭ ላይ ጫና ስለሚፈጠር እግራችን አካባቢ ህመም ሊሰማ እንደሚችል በወራቤ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሼላይዝድ ሆስፒታል የነርቭ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ኢልሀም አ/ሀኪም ያስረዳሉ።

የዲስክ መንሸራተት ምልክቶች ምንድን ናቸው?

እግር ላይ የማቃጠል ስሜት ፣ የእግር ስሜት ማጣት የመዛል፣ በምንቀመጥበት ጊዜ ከፍተኛ ህመም መሰማት እና በእንቅስቃሴ ጊዜ ደግሞ የህመም ስሜት መቀነስ፥ ዲስኩ የተንሸራተተው ወደ መሃል ከሆነ ዋናውን እስፓይናልኮርድ (የጀርባ አጥንት) ስለሚጫነው ሽንትና ሰገራ አለመቆጣጠርና መሰል ጉዳቶች ሊስተዋሉ እንደሚችሉም ነው ዶክተር ኢልሀም የሚገልጹት።

ለዲስክ መንሸራተት አጋላጭ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

በእንቅስቃሴና ተያያዥ ሁኔታዎች ከፍተኛ የወገብ እንቅስቃሴን የሚጠይቁና ከባድ እቃዎችን የሰውነታችንን ሚዛን ሳንጠብቅና ሳንዘጋጅ በምናነሳበት ወቅት መዛባት ሊፈጠር ይችላል።

በብዛት እንዲህ አይነት ስራ የሚሰራ ሰው ከጊዜ ብዛት እክሉ ሊያጋጥመው ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይመከራል፡፡

የእድሜ መጨመር፦ እድሜ እየጨመረ ሲሄድ አጥንታችን እየሳሳ እንደሚሄደው ሁሉ ዲስክም ከግዜ ብዛት ተለጣጭነቱን በማጣት ሊዛነፍ ስለሚችል እድሜም አንዱ አጋላጭ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

ተፈጥሯዊ ችግር፦ የአፈጣጠር ችግር ያለበት ሰው ዲስኩ ሊጎዳ የሚችል ሲሆን መሰል ምክንያቶች ዲስኩ ተጎድቶ በመዛነፍ ነርቭ ላይ ጫና የሚያሳድር ከሆነ የዲስክ መንሸራተት ህመምን ሊፈጥር ይችላል፡፡

ህክምናው ምን ይመስላል?

ታካሚው በሚሰማው የህመም ምልክቶች ላይ የተመሰረተ ምርመራ  የሚደረግ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ሁኔታው ከበድ እያለ ሲመጣ ኤም አር አይ በተሰኘ የህክምና መሳሪያ በመታገዝ የነርቮችን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ምርመራ ይከናወናል፡፡

ቀላል የህክምና ትዕዛዞች፡፦ ታካሚው እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ፣ ዋና እንዲዋኝ፣ ስፖርት እንዲሰራ የሚታዘዝ ሲሆን ማስታገሻ ሊታዘዝም ይችላል፡፡

በዚህ ለውጥ ሳይመጣ ከቀረ ህመሙ ወይንም ዲስከ መንሸራተት የተፈጠረበት አካባቢ ላይ ማስታገሻ ይሰጣል፡፡

በእነዚህ ሁኔታ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ በቀዶ ጥገና የተጎዳውን አካል በማስተካከል ህመሙም እንዲታገስ ማድረግና ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዳይደርስ ማድረግ ይቻላል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.