Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካውያን በፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት የህብረቱ አባል ሀገራት ጠንካራ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት ተጠያቂነትን ማስፈን እንዳለባቸው ተገልጿል።

ይህን የገለጹት በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽነር አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ ናቸው፡፡

የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት የአፍሪካውያን የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ምን መምሰል እንዳለበት የሚያስቃኝ “የበጀት ፖሊሲ ውይይት” መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽነር አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ÷ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እንዲሁም 2030 የልማት ግቦችን ለማሳካት የፋይናንስ ስርዓቱ መዘመን ይገባዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አፍሪካውያን በሀገራቸው የሚበጀተው በጀት ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ ጉዳዮች ላይ ፈሰስ መደረጉን መከታተልና መቆጣጠር አለባቸው ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የማይክሮ ኢኮኖሚና አስተዳደር ክፍል ዳይሬክተር አዳም ኢልሂራይካ(ዶ/ር) በአፍሪካ በየዓመቱ የሚስተዋለውን 200 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የበጀት ልዩነት ለማጥበብ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር መዘርጋት ይገባል ብለዋል፡፡

አፍሪካውያን ከሀገር ውስጥ ገቢ የሚሰበስቡት ገንዘብ የጠቅላላ በጀታቸውን 36 በመቶ ብቻ በመሆኑ የታክስ አሰባሰብ ስርዓታቸውን መፈተሽ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በአፍሪካ በተለይም በማዕድን ዘርፍ ተሰማርተው ከአስር ዓመት በላይ ቆይተው ምንም ዓይነት ግብር ሳይከፍሉ የቆዩና ከስረናል ብለው የሚወጡ ካምፓኒዎች ብዙ መሆናቸውን ገልጸው÷ በዚህ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት/ዩኒሴፍ/ የአፍሪካ ህብረትና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካይ ላይላ ጋድ(ዶ/ር) የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 አካታች ልማትና ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ በታዳጊዎች ላይ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም አፍሪካውያን በበጀት አጠቃቀማቸው ላይ ግልጽነትን በማስፈን የነገ ተስፋ የሆኑ ህፃናትን ታሳቢ በማድረግ ለሚሰሩት ስራ ሁሉ ዩኒሴፍ ከጎናቸው ይቆማል በማለት ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.