Fana: At a Speed of Life!

የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ስራ ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ለመመለስ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

በኮርፖሬሽኑ የትራንስፎርሜሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ ፍፁም ከተማ እንደገለጹት÷ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ያለበትን ደረጃ የሚከታተልና ወደ ስራ ለመመለስ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራ የሚሰራ ቡድን በመላክ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

አሁን ላይም ሙሉ በሙሉ ፓርኩን ወደ ሥራ ለመመለስ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከሰላም ስምምነቱ መፈረም በኋላ ኮርፖሬሽኑ ባደረገው ምልከታ ፓርኩ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስበት፣ የአምራች ባለሀብቶች ንብረት እና ማሽነሪዎች እንደነበሩ መገኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም ፓርኩን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት፣ የነበሩ ባለሀብቶችን ለመመለስ እና አዳዲስ ባለሀብቶችን ለማስገባት የተሰራውን ስራ ውጤታማ አድርጎታል ብለዋል፡፡

በፓርኩ ኢንቨስት አድርገው የነበሩ ባለሀብቶችን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት ከባለሀብቶቹ ጋር ውይይቶች መደረጋቸውንና ባለሀብቶቹም ፈቃደኞች መሆናቸውን አቶ ፍጹም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.