Fana: At a Speed of Life!

ዩክሬን ወደ ክሬሚያ በሚወስደው ድልድይ ላይ ጥቃት መፈፀሟን ሩሲያ ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩክሬን ወደ ክሬሚያ በሚወስደው የኮንሃር ድልድይ ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈፀሟን ሩሲያ ገልፃለች፡፡

“የክሬሚያ መግቢያ” በመባል የሚታወቀው ይህ ድልድይ ክሬሚያን ከሩሲያ እና ከደቡባዊ የኬርሰን ግዛት ጋር የሚያገናኝ ሲሆን በድልድዩ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ምክንያት የትራፊክ ዝውውሩ መስተጓጎሉ ነው የተገለፀው፡፡

ሩሲያ የኮንሃር መንገድ በሚል የምትጠራው ይህ ድልድይ የሩሲያ ጦር በክሬሚያ እና በቁጥጥሩ ስር ባሉ ሌሎች የዩክሬን ግዛቶች ለመንቀሳቀስ የሚጠቀምበት መንገድ እንደሆነ ሬውተርስ በዘገባው አመላክቷል።

በጉዳዩ ላይ ኬቭ እስካሁን ምንም አይነት ማስተባበያ አለመስጠቷንም ነው ዘገባው ያመላከተው፡፡

ሩሲያ በተቆጣጠረችው የኬርሰን ግዛት አስተዳዳሪ ቭላድሚር ሳልዶ፥ በጥቃቱ ድልድዩ መጎዳቱን ተናግረዋል።

ድርጊቱ የኪየቭ ወታደሮች የኬርሰን ነዋሪዎችን ለማስፈራራት እና በህዝቡ መካከል ድንጋጤን ለመፍጠር በማሰብ ያደረጉት መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህ እንደማይሳካለቸው እና መንገዱ በቅርቡ ተጠግኖ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡

በጠላት ለሚደረገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ መልስ አለን ያሉት አስተዳዳሪው፥ በመንገዱ መጎዳት ምክንያት የትራፊክ መስተጓጎል እንዳይኖር ተቀያሪ መንገድ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.