Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ 7ኛው ዙር ከተማ አቀፍ የንባብ ባህል ሳምንት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ 7ኛው ዙር ከተማ አቀፍ የንባብ ባህል ሳምንት “ንባብ ለዘለቄታዊ ልማት ” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ፣ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና ላይ መሆኗን አንስተው÷ ልማቱን ለማስቀጠልም የለማ አዕምሮ ማፍራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህም ንባብ ትልቁ መሳሪያ መሆኑን ለማሳየት እና የኢትዮጵያን ልማት ለማፋጠን በየሩብ ዓመቱ የንባብ ባህል ሳምንት እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

መርሐ ግብሩ መልካምና እውቀት የታጠቀ ዜጋ መፍጠር ላይ የተመሠረተ ተግባር ለመፈጸም ንባብ ትልቅ መሠረት መሆኑን ለማስረፅ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው÷ የሰው ልጅ ካነበበ ሁሉንም መሆን ይችላል፤ ንባብ የአዕምሮ ምግብ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱም የተገኙት የክብር እንግዶች የመጽሐፍት አውደርዕይን በይፋ ማስጀመራቸውን የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡

ለሦስት ተከታታይ ቀናቶች በሚደረገው የንባብ ባህል ሳምንት ፌስቲቫል ላይም በተማሪዎች መካከል የሚደረጉ የንባብ ባህልን ለማጎልበት የሚረዱ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.