Fana: At a Speed of Life!

ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በመኖሪያ ቤታቸው ያከማቹ 13 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያና ከ100 ግራም ወርቅ በላይ በመኖሪያ ቤታቸው ያከማቹ 13 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳ እንደሆነ የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በዚህም ከ100 ግራም ወርቅ በላይ፣ ሁለት የወርቅ ማዕድን መፈለጊያ ማሽን፣ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ፣ ሰባት ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ ስድስት ሽጉጥና በርካታ ጥይቶች ተጠርጣሪዎቹ ይዘው በመገኘታቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ነውም ብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ የማዕድን ግብይት አዋጅ ቁጥር 1144/2011 የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ በሕገ-ወጥ መንገድ የወርቅ ማዕድን በመኖሪያ ቤታቸው በማስቀመጥ ለግል ጥቅማቸው ሊያውሉ ሲሉ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ነው ፖሊስ የገለጸው፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከህብረተሰቡ ባገኙት መረጃ መሰረት በመኖሪያ ቤታቸው ባደረጉት ፍተሻ ሊደረስባቸው መቻሉም ነው የተጠቆመው፡፡

በመሆኑም ÷በመሰል የወንጀል ድርጊቶች የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖችን በማጋለጥ አሳልፎ ለፀጥታ አካላት በመስጠት ኅብረተሰቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.