Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሀገራት የቀጣናዊ ትብብር በማጠናከር የታዳሽ ሀይል ሽግግርን ማሳለጥ እንደሚገባቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሀገራት ሀብቶቻቸውን በማሰባሰብ ቀጣናዊ ትብብር እና አጋርነትን በማጠናከር የታዳሽ ሀይል ሽግግርን ማሳለጥ እንደሚገባቸው ተገለጸ፡፡

በኬንያ ናይሮቢ በፈረንጆቹ ከሰኔ 20 ቀን 2023 ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የኢነርጂ ፎረም ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ተገኝተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ባሻገር የአፍሪካ ሀገራት ሀብቶቻቸውን በማሰባሰብ ቀጣናዊ ትብብር እና አጋርነትን በማጠናከር የታዳሽ ሀይል ሽግግርን ማሳለጥ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ያመጣል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ የተለያዩ የታዳሽ ሀይል የማመንጨት አቅም ቢኖርም 600 ሚሊየን አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንደማያገኙ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ከ60 ሚሊየን በላይ ዜጎች የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አብዛኞቹ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለዘላቂ ኢነርጂ አቅርቦት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ የሚታየውን የኢነርጂ አቅርቦት እጥረት ለማስቀረት የሀገር ውስጥ የመንግስት ፋይናንስ አቅርቦት፣ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት እንዲሁም የልማት አጋሮች ያልተቋረጠ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኢትዮጵያ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ለማቅረብ ጭምር በመድረኩ መገኘታቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በመድረኩ 24 የሚሆኑ የተለያዩ ሀገራት የዘርፉ ሚኒስትሮች፣ የሀገራት ተወካዮችና የግሉ ዘርፍ እየተሳተፉ እንደሚገኙ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.