Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የሰላም ልኬት የሙከራ ጥናት ውጤት ማብሰሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የሰላም ሚኒስቴር ኢንተር ፒስ ከተባለ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ ከሚሰራ ዓለም አቀፍ ተቋም ጋር በመተባበር ያስጠናውን ”የኢትዮጵያ የሰላም ልኬት የሙከራ ጥናት ወጤት ይፋ አደረገ፡፡

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ለአንድ ሀገር ሰላም መረጋገጥ ጠንካራ ተቋማት እና ስርዓት መገንባት ወሳኝ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የህዝቦች ንቁ ተሳትፎና ፈተናን ተቋቁሞ የማለፍ አቅም ለዘላቂና አስተማማኝ ሰላም መሠረት ስለመሆኑም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ ልሂቃን ውስብስብ ፍላጎት እና የዕርስ በዕርስ መገፋፋት የሚፈጠሩ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ተቋቁመው የቆዩ ህዝቦች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህን ጥንካሬና ፅናት በጥናት በተደገፉ አሰራሮች ማጠናከር እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

ዛሬ ይፋ የተደረገው የሰላም ልኬት የሙከራ ጥናት ውጤት የሰላም ሚኒስቴር በጥናትና በመረጃ የተደገፈ ስራን ለመስራት እና በሀገራችን ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚረዱ ስራዎችን ለመስራት ትልቅ ግብዓት እንዲሆን የተጀመረ የሙከራ ጥናት ውጤት ነው ብለዋል፡፡

የኢንተርፒስ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳይመን ጊምሰን በበኩላቸው÷ ተቋማቸው በዘላቂ ሰላምና አብሮነት ላይ ከሚሰሩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ያስጠናው የሰላም ልኬት የሙከራ ጥናትም የዚህ አንድ አካል መሆኑን አንስተዋል፡፡

የጥናቱ ዓላማ ሰላምን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመረዳት የሚያስችል በሳይንሳዊ መንገድ የተሰበሰበና የተተነተነ መነሻ መረጃ እንዲኖር እና ለችግሮች ሳይንሳዊ መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡

የሰላም ልኬት የሙከራ ጥናት በደቡብ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ በሲዳማ ክልል እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውስጥ የተጠና መሆኑን የሰላም ሚኒስር መረጃ ያመላክታል፡፡

ጥናቱን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ለማካሄድ ቢታቀድም በነበረው ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ምክንያ አለመሳካቱ ተጠቅሷል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ታዬ ደንደአ በዚህ ጥናት የተገኙ ውጤቶች ለሌሎች ጥናቶች እንደ መሣሪያ እንደሚያገለግሉ ጠቅሰው÷ ይህ ጥናት ማን የት ቦታ ምን መሠራት እንዳለበት የሚያመለክት ነው ብለዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.