Fana: At a Speed of Life!

ፖሊስ በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍተዋል ያላቸውን 20 ግለሰቦች ፍርድቤት አቀረበ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ፖሊስ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ ከደብረ ብርሃን በቅርብ ዕርቀት ላይ በሚገኝ መኖሪያ ቤት በመመሸግ በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍተው ነበር ያላቸውን 20 ግለሰቦች ፍርድቤት አቀረበ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ያቀረበውን ጥርጣሬ መነሻ ምክንያቶችና በተጠርጣሪ ጠበቆዎች በኩል የተነሱ የመከራከሪያዎችን ተመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ አጠቃላይ 20 ሲሆኑ አራቱ ሴቶች ናቸው።

ከተጠርጣሪዎች መካከል የቀድሞ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባል ነበሩ የተባሉት ም/አ/ አለቃ ታጠቅ ማሞ፣ኮ/ብል ሽፈራው ሀይሉ፣ ረ/ሳጅን አብርሐም ኃይለ እየሱስ፣ መስፍን ጣልአርጌ፣ኮ/ብል ቃሉ ግዛቸው፣ኮ/ብል ጌታሁን ካሀብይመር ፣ኮ/ብል ጌታሁን መኮንን እና ም/አ/አለቃ እንዳሻው ግርማ ይገኙበታል።

ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል አራቱ የልዩ ኃይል አባል ያልነበሩ ናቸው ተብሏል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ተጠርጣሪዎቹን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍልና በተለይም በአማራ ክልል የብሔር ፖለቲካ ፅንፈኝነትን መሰረት አድርገው ህገ -መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስና ሽብር ለመፍጠር በማቀድ ፣በህቡዕ ታጣቂ ኃይል በማደራጀት፣የጦር መሳሪያ በመታጠቅ እንዲሁም በትጥቅ የታገዘ ህዝባዊ እንቢተኝነት በመቀስቀስ የተረጋጋ መንግስትና ኃይል እንዳይኖር ፣መዋቅሩን ለማወክ ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከደብረ ብርሃን ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ሳሪያ ሚካኤል ቀበሌ ልዩ ቦታው ኩክ የለሽ ገዳም ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መሽገው ነበር በማለት ለችሎቱ አስታውቋል።

ፖሊስ አክሎም ተጠርጠሪዎቹ 1 ዲሽቃ፣ ከ501 ጥይት ጋር፣ አራት ስናይፐር፣ ሁለት ብሬን ከ1 ሺህ 348 ጥይቶችጋር፣ ሁለት ሽጉጥ ሶስት F1 የእጅ ቦምብ፣አምስት ክላሽ ከመሰል 530 ጥይቶች ጋር በመታጠቅ መሽገው ነበር በማለት ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ በ13ኛ ተጠርጣሪ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ መሽገው ነበር በማለት የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ በወቅቱ የወረዳው የፀጥታ አካላትና ሚኒሻዎች ፀጉረ ልዉጥ እና የታጠቁ ሰዎች ይንቀሳቀሳሉ የሚል ጥቆማ ደርሷቸው ወደ መሸጉበት መኖሪያ ቤት ምን እየሰሩ እንደሆነ ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት ተጠርጣሪዎቹ በከባድ ጦር መሳሪያ ተኩስ በመክፈት ውጊያ በመግጠማቸው ምክንያት ሚኒሻዎቹም መከላከያ ሰራዊት በመጥራት ከእነ ጦር መሳሪያቸው በሰኔ 15 ቀን 2015ዓ.ም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተድርገዋል በማለት የጥርጣሬ መነሻውን ዘርዝሮ ለችሎቱ አስረድቷል።

በዚህም መነሻ ሰኔ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተጠርጣሪዎችን ከመከላከያ በመረከብ ምርመራ ማጣራት መጀመሩን የገለፀው መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሰው ምስክርና የሰነድ ማስረጃዎችን ሰብስቦ ለመቅረብ እንዲያስችለው በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 59/1 መሰረት የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ተጠርጣሪዎቹ ለእረፍት ወደ ቤተሰብ ጋር ከሄዱ በኋላ አድማ ብተና ውስጥ ትቀላቀላላችሁ ተብለው እየተጠባበቁ በነበሩበት ወቅት ነው የተያዙት በማለት የፖሊስን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄውን ተቃውመዋል።

የሽብር ወንጀል ድርጊት ለመፈጸም የተያዙ አይደለም ያሉት ጠበቆቹ ፖሊስ ያቀረበው ምክንያታዊ የጥርጣሬ መነሻ የለውም በማለት ተከራክረዋል።

በተጨማሪም 13ኛ፣16ኛ፣19ኛ እና 21ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ግለሰቦች የልዩ ኃይል አባል እንዳልሆኑ የጠቀሱት ጠበቆቹ የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት እንዲከበርም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ ተቀምጠው ነው የተያዙት ለሚለው የጠበቆች መከራከሪያ ነጥብን በሚመለከት መልስ የሰጠው መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ በኩክ የለሽ ገዳም አቅራቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ጋር በመመሳሰል በ13ኛ ተጠርጣሪ ቤት መሽገው እንደነበርና በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍተው መያዛቸውን በመጥቀስ መልስ ሰጥቷል።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ መንግስት በየዘርፉ እንዲቀላቀሉ ለክልሉ ልዩ ኃይል ጥሪ ባስተላለፈበት ወቅት ተጠርጣሪዎቹ አንቀበልም ብለው ከኢ -መደበኛ አደረጃጀት ጋር በመቀላቀል ከተለያዩ ወረዳዎች በመጠራራት ተሰባስበው ነው ይህን ድርጊት የፈጸሙት በማለት በማብራራት መልስ ሰጥቷል።

ፖሊስ አክሎም ተጠርጣሪዎቹ እጅ ላይ የተያዙ የጦር መሳሪያዎችን በሚመለከት በክልሉ መንግስት ምንም መሳሪያ እንዳላስታጠቃቸው በመግለፅ መሳሪያውን ገዝቶ ያስታጠቃቸው የሎጀስቲክ ፈንድ የሚያደርግላቸው አካል መጣራት እንዳለበት ገልጾ መልስ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል አንደኛው ጠበቃ ተጠርጣሪዎቹ መሳሪያ ከፊታቸው ተቀምጦ ፎቷቸው ተለጥፎ ንፁህ ሆነው የመገመት መብታቸውን በጣሰ ሁኔታ በመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ተሰርቷል ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል። እንደአጠቃላይ የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ ለመስጠት ለፊታችን ሀሙስ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.