Fana: At a Speed of Life!

የኔቶ አባል ሀገራት በዋግነር ጦር ጥቃት ይደርስብናል የሚል ሥጋት አይግባችሁ – ኔቶ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትናንትናው ዕለት የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ኃይል ቤላሩስ መግባቱን ተከትሎ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) አባል ሀገራቱን ጥቃት ይደርስብናል የሚል ሥጋት እንዳይገባቸው አሳሰበ፡፡

የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ÷ የምዕራባውያኑ ወታደራዊ ጥምረት ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት ራሱን ለመከላከል በተጠንቀቅ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የዋግነር ጦር በትናንትናው ዕለት በይፋ ከሩሲያ ወደ ቤላሩስ መግባቱን ማስታወቁን ተከትሎ ÷ የምሥራቅ አውሮፓ የኔቶ አባል ሀገራት በቀጣናው አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል የሚል ሥጋት እንደገባቸው አልጀዚራ ዘግቧል።

የሊትዋኒያ ፕሬዚዳንት ጊታናስ ናውሴዳ ከኔቶ ዋና ጸሐፊ ስቶልተንበርግ እና ከሌሎች ስድስት የኔቶ አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር በሄግ ከተገናኙ በኋላ ÷ “የዋግነር ጦር በቤላሩስ ገዳዮችን ቢያሰማራ ሁሉም ጎረቤት ሀገራት ከባድ ሥጋት እና አለመረጋጋት ውስጥ ይወድቃሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

የፖላንድ ፕሬዚዳንት አንድርዜጅ ዱዳ ÷ “በፈረንጆቹ የፊታችን ሐምሌ 11 እና 12 በቪልኒየስ፣ ሊቱዌኒያ በሚካሄደው የ31 የኔቶ አባል ሀገራት ጉባዔ ላይ የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ኃይሎች ጉዳይ በሥጋትነት የሚታይ አጀንዳ እንደሚሆን ተሥፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

አባል ሀገራቱ ጉዳዩን በአንክሮ ተመልክተው ጠንካራ ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳለባቸውም ከወዲሁ አሳስበዋል፡፡

ጄንስ ስቶልተንበርግ ÷ የዋግነር ጦር ገና ለገና ቤላሩስ ገባ ብሎ ይሄን ያኅል መሥጋት አግባብ እንዳልሆነና ኔቶ የእያንዳንዱን አባል ሀገር ግዛት እያንዳንዷን ኢንች ከሥጋት እንደሚጠብቅ አረጋግጠዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.