Fana: At a Speed of Life!

ዓለም እያጋጠማት ያለውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ብዝሃነትን መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የመፍትሄ አማራጮች ያስፈልጋሉ – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም እያጋጠማት ያለውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ብዝሃነትን መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የመፍትሄ አማራጮች እንደሚያስፈልጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት (ኦኢሲ) በአዲስ አበባ እያካሄደ ባለው የመጀመሪያው ልዩ ጉባዔ ላይ እየሳተፉ ነው።

ላለፉት ሁለት ቀናት በሚኒስትሮች ደረጃ ሲካሄድ የቆየው ልዩ ጉባዔ የድርጅቱ አባል አገራት መሪዎች ስብሰባ ዛሬ ተጀምሯል።

በጉባዔው የደቡብ ለደቡብ ትብብር ማዕቀፍን ለማጠናከር፣ በትምህርቱ ዘርፍ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና አጋርነትን መሰረት ያደረገ አዲስ የባለ ብዙ ወገን ትብብር መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የፖሊሲ ውይይቶች ተደርገውበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባዔው ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ኢትዮጵያ የድርጅቱ ዓላማዎች እንዲሳኩ የበኩሏን ሚና እንደምትወጣ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ አካታች የሆነ የትምህርት ስርዓትን በመከተል በተለይ በዘርፉ ሁሉም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ትምህርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ዓለምን በበጎ መልኩ ለመቀየር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷መፍትሄ ተኮር በሆኑ የምርምር ስራዎች በትብብር መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡

ትናንት በልዩ ጉባዔው ሁለተኛ ቀን ውሎ የድርጅቱ አባል አገራት በውይይታቸው ተቋሙ ካስቀመጠው ተልዕኮ አንጻር ሊሳካ የሚችል የስም ስያሜን በተመለከተ መክረዋል።

በዚሁ መሰረት ጠቅላላ ጉባዔው ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት ስያሜው ደቡብ ንፍቀ ክበብ አገራት ትብብር ድርጅት በሚል እንዲቀየር ውሳኔ ማስተላለፉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የድርጅቱ የወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው በመጠናቀቁ ለኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ ኃላፊነታቸውን ማስከረከባቸው ይታወቃል።

ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት (ኦኢሲ) በፈረንጆቹ ጥር 2020 የተቋቋመ ሲሆን÷ ከአፍሪካ፣ እስያ፣ ፓሲፊክ፣ ላቲን አሜሪካ፣ ካሪቢያን እና የአረቡ ዓለም አገራትን በአባልነት ያቀፈ ነው።

ድርጅቱ ሚዛናዊ፣ አካታች እና ሁሉን አቀፍ የትምህርት ስርዓት በመዘርጋት በእኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና አጋርነት ላይ የተመሰረተ ልማት ማምጣትን አላማ አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የተቋሙ መስራች አባል እና ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫም ናት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.